
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር
ከቲሊሊ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሕዝብን ለከፋ ችግር እና ጉዳት መዳረጉን ተናግረዋል። ቲሊሊ ከተማ በጽንፈኛው ቡድን ተደጋጋሚ ጉዳት እንደደረሰባትም ገልጸዋል።
ከውጭ ጠላት ሳይመጣ በውስጥ የተነሱ ታጣቂዎች ሕዝብን ለከፋ ስቃይ መዳረጋቸውንም ተናግረዋል። የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ባሉበት ሀገር በግጭት ውስጥ መቆየት እንደማይገባም አንስተዋል።
በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎችን መመለስ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ሁሉም ውገን ግጭት በቃን ብሎ መነሳት አለበት ነው ያሉት። ግጭቱ እንዲነሳ፣ እንዲባባስ እና እንዲራዘም ያደረጉ ኃይሎች አሉ፤ አሁንም ጽንፈኛውን በመረጃ እና በመገንዘብ የሚደግፉ አሉ ነው ያሉት።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ጽንፈኛውን በድፍረት ማውገዝ እና መታገል ያስፈልጋል ብለዋል። በልማት የሚታወቀው አካባቢ የግጭት ቀጣና ሲኾን ያሳዝናል፤ ለግጭቱ መነሻ ደግሞ ሁላችንም አስተዋጽኦ ነበረን፤ ግጭቱ ሁላችንም ጎድቷል፣ ለሰላሙም ሁላችንም አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን ነው ያሉት።
ጽንፈኛው ቡድን እየተበተነ እና እየፈረሰ ነው፤ ይሄን እየፈረሰ ያለውን ቡድን ማጽዳት ደግሞ ከሁሉም ይጠበቃል ነው ያሉት። ግጭትን የሚያወግዙ እና ግጭት እንዳይፈጠር የሚመክሩ የሃይማኖት አባቶች እንዳሉ ሁሉ ግጭትን የሚያባብስ የሃይማኖት አባቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም መኾኑንም ገልጸዋል። መንግሥት እየተጠቀመው ያለውን የሰላም አማራጭ አጠናክሮ እንዲቀጥም ጠይቀዋል። ሕዝብን እያማረሩ የሚገኙ የአግልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ መቁረጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ሁለት ቦታ እየረገጡ እና እያወላወሉ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ አይቻልም ነው ያሉት። ጽንፈኝነትን መደገፍ የጉስቁልና ጊዜን ያራዝማል እንጂ ሰላምን አያመጣም ብለዋል።
የትርፍ አምራች፣ የሰላም እና የትብብር፣ የእርቅ እና የፍቅር ተምሳሌት የኾነው አካባቢ በጸጥታ ችግር ውስጥ ሲገባ ያሳዝናል ነው ያሉት። በእናንተ የሚያምረው ለእርቅ እና ለሽምግልና መመለስ ነው ብለዋል።
እርስ በእርስ በመገዳደል የሚመጣ ሰላም እንደሌለም ተናግረዋል። ክብራችሁን የሚመጥነው በቆዬው ባሕል እና እሴት ዘላቂ ሰላምን መመለስ እንጂ ወንድም ወንድሙን ሲገድለው ዝም በማለት አይደለም ብለዋል። ገዳይን፣ ዘራፊን እና ወንበዴን ማጀገን ለታሪክም ኾነ ለባሕል አይመጥንም ነው ያሉት።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ዝም ካሉ የሀገር በሽታ አይታከምም፤ ዘላቂ ሰላምም አይረጋገጥም ብለዋል።
ሕዝብን እያሰቃየ በሚገኘው ጽንፈኛ ቡድን ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከለካያ ሠራዊት የኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ መሐመድ ኢትዮጵያ ታላቅ እና የጥንት ታሪክ ያላት፣ ለሌሎች ሰላም የቆመች እና የተዋደቀች፣ ነጻነቷን አስጠብቃ የኖረች ሀገር ናት ብለዋል። አኩሪ ታሪክ ያላት ሀገርን ይዘን ለምን ሰላም አጣን ? የሚለውን መመርመር እና ለሰላም መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያ ሰላም እንዳትኾን እና እንዳታድግ እንደሚሠሩም ገልጸዋል። እርስ በእርስ መጋጨት ሀገርን ለጠላት አሳልፎ መስጠት እና የጠላትን ግብ ማሳካት ይኾናል ነው ያሉት። ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የውስጥ ሰላምን ማረጋገጥ እና አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባም አመላክተዋል።
በጀግንነት ስትጠበቅ የኖረች ሀገር በእኛ ዘመን ጠላት እንዲያፈርሳት አንፈቅድም፤ እናንተም የጠላት መሣሪያ አትሁኑ ነው ያሉት። በአማራ ክልል ያለው ጽንፈኛ ቡድን የአማራ ሕዝብን ጥያቄ የሚያስፈታ አይደለም፤ ይልቅስ ጥያቄዎቹ እንዳይፈቱ እንቅፋት የሚኾን፤ ከጠላቶቹ ጋር የሚሠራ፣ ስቃዩን የሚያበዛ ዘራፊ እና ተላላኪ ነው ብለዋል።
ልጆችን የሚያግት፣ እንዳይማሩ የሚከለክል፣ ንጹሐንን የሚገድል ጽንፈኛ ቡድን ለሕዝብ አይጠቅምም ነው ያሉት። ጽንፈኛውን የሚደግፍ ሁሉ ከደርጊቱ መቆጠብ እንደሚገባውም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በግጭት አዙሪት ውስጥ ላለመቆየት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ይጠበቅባችኋል ብለዋል። “የእናንተን ሰላም ከእናንተ በላይ የሚጠብቀው የለም”፤ የልማት ጥያቄዎች እንዲፈቱ ሰላማችሁን ማረጋገጥ አለባችሁ
ነው ያሉት።
ጽንፈኛው ቡድን ሕዝብን የሚዘርፍ፣ የሚቀማ፣ የሚያግት፣ የሚገድል እና ንብረት የሚያወድም መኾኑንም ተናግረዋል። ብልሕ፣ አስተዋይ፣ ሃይማኖተኛ እና ጸሎተኛ ሕዝብ ችግሮችን በሐቅ እና በስክነት ይፈታል ነው ያሉት።
አስተዋይ ሕዝብ የችግሮችን ሥረ መሠረት ይፈልጋል፤ አይደናገርም፤ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ይሠራል፤ ሰላም በቅድመ ሁኔታ ይረጋገጣል ብሎ አያምንም፤ የችግሮችን አካሄድ አስቀድሞ በመረዳት ጉዳት እንዳይደርስ ይከላከላል፤ እሳት እንዳይነሳ ያደርጋል ብለዋል።
ብልሕ ሐቅን የሚናገር፣ የሚመክር እና የሚዘክር መኾኑንም ተናግረዋል። ጽንፈኛው ቡድን የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች እንዳይመለሱ የሚሠራ የታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ መኾኑንም ገልጸዋል። ከግብጽ፣ ከሻቢያ እና ከሕወሐት ጋር የሚሠራ ጽንፈኛ ቡድን የሕዝብ ጥያቄን ሊያስመልስ አይችልም ነው ያሉት።
የጽንፈኛው ቡድን ዓላማ ሥልጣንን በኃይል መያዝ ነው፤ ይህ ዓላማው ግን ከሽፏል ብለዋል። ጽንፈኛው ቡድን የጠላት ተላላኪ፣ ከጠላት ጋር የተሰለፈ፣ ዘራፊ እና አውዳሚ መኾኑንም ተናግረዋል።
ሰላምን ለማረጋገጥ የሰላም አማራጭን በማስቀደም መሠራቱን ገልጸዋል። በተፈጠረው የሰላም አማራጭ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል ነው ያሉት።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለእውነተኛ ሰላም እንዲሠሩ፣ በግልጽ እንዲያውግዙ እና እንዲገስጹ ጠይቀዋል። ውስጣዊ አንድነት እና ሰላም እንዲመጣ እንዲሠሩም አስገንዝበዋል።
ከችግር ለመውጣት ለዘላቂ ሰላም መሥራት እና ሐቅን ይዞ መታገል እንደሚገባም ተናግረዋል። ሽፍታን መንከባከብ ለሀገር እና ለሕዝብ እንደማይጠቅምም አመላክተዋል። ለራሳቸው ሰላም እንዲሠሩም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
