በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርት ለማግኘት ታቅዷል፡፡

490

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለሰሊጥ አምራቾች የገበያ ችግር ይፈጥራል የሚል ስጋት መኖሩን የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ በሰሊጥ ምርት ከሚታወቁ አካባቢዎች ምዕራብ ጎንደር ዞን ተጠቃሽ ነው፡፡ በዞኑ በ2012/13 የምርት ዘመን 184 ሺህ 345 ሄክታር መሬት ላይ ሰሊጥ ለመዝራት ታቅዷል፡፡ በሄክታር ስምንት ኩንታል ሰሊጥ ይገኛል ተብሎ እንደታሰበም የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡ ከአጠቃላይ ምርቱ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰሊጥ ለማግኘት እየተሠራ እንደሆነም ታውቋል፡፡

በቂ የአፈር ማዳበሪያ መቅረቡንና በግብርና ምርምር እና በአርሶ አደሮች የተባዙ ምርጥ ዘሮች መሰብሰባቸውም ዕቅዱን ለማሳካት መልካም አጋጣሚ እንደሚሆኑ ታምኗል፡፡ ለአብነትም በመተማ አካባቢ ለሰሊጥ ምርት “አባሲኒያ” የተሰኘ ምርጥ ዘር፣ በምዕራብ አርማጭሆ ደግሞ “ሂርሂር” ተፈላጊዎች እንደሆኑ የመምሪያ ኃላፊው አቶ ጌትነት በሊሁን ገልጸዋል፡፡

የሰሊጥ አመራረት በባሕርይው የሰው ኃይል በብዛት እንደሚፈልግ የተናገሩት አቶ ጌትነት በየዓመቱ ከአማራ ክልልና ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጣ ከ800 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ሰው በሥራው ይሣተፍ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ዘንድሮ ግን በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሰው ኃይል እጥረት ይገጥማል የሚል ስጋት መኖሩን ነው የተናገሩት፡፡

ሰሊጥ ከኢትዮጵያ የሚያስገቡ እንደ ቻይና እና ኔዘርላንድ ያሉ ሀገራት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በቀጣይ ዓመት ላይሸምቱ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ በአርሶ አደሮች በኩል መፈጠሩም ሌላው ስጋት ነው፡፡ በ2011/12 የምርት ዘመን አርሶ አደሮች ካወጡት ወጪ አንፃር ያልተመጣጠነ በአማካይ በሄክታር ሦስት ኩንታል ሰሊጥ ምርት ከመገኘቱ ባሻገር አንዱን ኩንታል በ4 ሺህ ብር ሒሳብ በመሸጥ ለኪሳራ መዳረጋቸው የዚህን የምርት ዘመን ስጋት ከፍ እንዳደረገውም ነው ያስታወቁት፡፡

አብመድ ከዚህ ቀደም በተከታታይ ዘገባዎቹ እንዳመላከተው ደግሞ ግዙፍ የዘይት ፋብሪካዎች በአማራ ክልል ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ነው፤ ለአብነትም በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ እና በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ማርቆስ እየተገነቡ የሚገኙ ፋብሪዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ፋብሪካዎቹ ከፍተኛ መጠን ያለው የቅባት እህል በግብዓትነት የሚጠቀሙ ናቸው፤ ይህም ምቹ የገበያ ትሥሥር እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታም በዓለም ገበያ የዋጋ መውረድ ያጋጠመው በኢንዱስትሪ ምርቶች እንጅ በግብርና ምርቶች ላይ አይደለም፡፡

ፎቶ፡- ከክምችት

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleየኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚገኙ ከ80 በመቶ በላይ ሆቴሎች በአብዛኛው ሥራ ማቆማቸውን መንግሥት አስታወቀ፡፡
Next articleእንጂባራ ዩኒቨርሲቲ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡