
ደባርቅ: ታኅሣሥ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ እና የሰሜን ጎንደር ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ በጋራ በግጭት አፈታት ዙሪያ በዞኑ ለሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች ሥልጠና ሰጥተዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ አስራት ክብረት “ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች ሀገራዊ ዕሴቶችን ለማስቀጠል እና ማኅበራዊ ቀውሶችን ለመፍታት ጠቀሜታቸው የጎላ ነው” ብለዋል።
የሀገር ሽማግሌዎችን መማክርት ጉባዔ በመመሥረት ወጥ የኾነ የአደረጃጀት መዋቅር ማሻሻል መቻሉንም ገልጸዋል።
የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ማኅበረሰብ ዓቀፍ አገልግሎቶች ዳይሬክተር ጌታቸው ውለታው ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ የሽምግልና ሥርዓቶች ያላቸውን ማኅበረሰባዊ ተቀባይነት በመገንዘብ ለማጠናከር እየተሠራ ነው ብለዋል።
በሥልጠና፣ በኢኮኖሚ እና በሌሎች ጉዳዮች ተቀራርቦ በመሥራት ትርጉም ያለው ለውጥ ለማስመዝገብ መታቀዱንም አብራርተዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው በግጭት አፈታት ዙሪያ ሥልጠና መሰጠቱ ግንዛቤን ለማሳደግ እና የላቀ ተገባር ለማከናወን አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
በቀጣይም ተመሳሳይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
