
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የ1447ኛውን ዓመተ ሂጅራ የሐጂ ምዝገባን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የከፍተኛ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አሕመድ ካሣ ሙዘይን ለመላው ሙስሊም እንኳን ለ1447ኛው ዓመተ ሂጅራ የሐጂ ምዝገባ አደረሳችሁ ብለዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2018 ዓመተ ልደት የሐጂ ምዝገባ ከሕዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች የምዝገባ ጣቢያዎች መጀመሩን ገልጸዋል።
በአማራ ክልልም በባሕር ዳር፣ በደሴ እና በከሚሴ የሐጂ ምዝገባ ጣቢያዎች ተጀምሯል ነው ያሉት። ሐጂ ከእስልምና መሠረቶች ውስጥ አንዱ በመኾኑ ሐጂ የማድረግ ግዴታ ያለባቸው ሙስሊሞች መስፈርቱን በማሟላት በምዝገባ ጣቢያዎቹ ቀርበው እንዲመዘገቡ አሳስበዋል።
ለሐጂ የሚመዘገቡ ሙስሊሞች ጉርድ ፎቶ ግራፍ፣ ፓስፖርት፣ የቢጫ ወባ ክትባት፣ የልደት ካርድ እና ከጤና ተቋማት ሜዲካል ሰርተፍኬት መያዝ እንዳለባቸውም በመግለጫው ጠቅሰዋል። የዘንድሮ የሐጂ ጉዞ ክፍያ 740 ሺህ ብር እንደኾነም ተገልጿል።
ማንኛውም ሐጂን መፈጸም የፈለገ ሰው ከሚከተሉት አሥር በሽታዎች ነጻ መኾን አለበት።
ምዝገባውም እስከ ጥር 18/2018 ዓመተ ልደት ድረስ ብቻ በመኾኑ ሐጂ ለማድረግ ያሰቡ ሙስሊሞች እየቀረቡ እንዲመዘገቡ ጥሪ ተላልፏል።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ኑረዲን ቃሲም ባስተላለፉት መልዕክትም ሙስሊሞች ብዙ ተጉዘው እና ኖረው ሐጂን ይፈጽሙ እንደነበር አስታውሰዋል።
ገንዘቡ እና አቅሙ ላላቸው ሰዎች ሐጂ ግዴታ መኾኑንም አሏህ በቁርዓን ያስቀመጠው ነው ብለዋል። ሐጂን ብዙ ቱሩፋቶች ያሉት የእስልምና መሠረት ነው ያሉት ሼህ ኑረዲን ገንዘቡን በአግባቡ ተጠቅሞ ሐጂ ያደረገ ሰው እናቱ እንደወለደችው ሐጥያት እንደሌለበት ሰው ኾኖ እንደሚመለስ ሰለላህ አለሂ ወሰለም እንደተናገሩት ገልጸዋል።
ሐጂን የሚፈጽሙ ሰዎች የአሏህ ልዑካን ቡድኖች ኾነው እንደሚቆጠሩም ገልጸዋል። በሐጂ ሙስሊሞች በአንድነት በአረፋ ተራራ ላይ ለተመሳሳይ ተግባር፣ ተመሳሳይ ለብሰው፣ ተመሳሳይ እየተናገሩ በአንድ ቦታ ተሰባስበው የሚገኙበት ቦታ ነው ብለዋል።
“ሐጂ ማድረግ የሚያከስር ሳይኾን ሃብትንም የሚያበረክት” መኾኑን ተናግረዋል። እናም አቅሙ ያላቸው ሙስሊሞች ሐጂን እንዲተገብሩ አበረታትተዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
