
ደሴ: ታኅሣሥ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን የደሴ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከዞን እና ከወረዳ ለተውጣጡ የግብርና ባለሙያዎች እና መሪዎች እንዲኹም ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ ከደቡብ ወሎ ዞን፣ ከሰሜን ወሎ እና ከኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከግብርና፣ ከማኅበራት እና ከፍትሕ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች እና መሪዎች ተሳታፊዎች ነበሩ።
በመድረኩ የግብርና ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የፀረ ተባይ እና የማዳበሪያ ሥርጭት ለአርሶ አደሮች በወቅቱ የመድረስ ችግር መኖሩ ተነስቷል።
ይህንን ችግር ይፈታል የተባለለት የተሻሻለ የፀረ ተባይ እና ማዳበሪያ ሥርጭት መመሪያ ትውውቅም ተደርጓል። ዘርፉ የሚጠበቅበትን ውጤት እንዳያመጣ ሕገ ወጥ የፀረ ተባይ እና የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት እንቅፋት መኾኑ የተመላከተ ሲኾን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የባለ ድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መኾኑም ተገልጿል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ ተሳታፊዎች እንደገለጹት የፀረ ተባይ እና የአፈር ማዳበሪያ ሕገ ወጥ ዝውውር በየአካባቢያቸው መኖሩን ተናግረዋል። የተሻሻለው መመሪያ ችግሩን ለመቅረፍ አጋዥ መኾኑንም ገልጸዋል።
በዘረፉ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ የፀረ ተባይ እና የአፈር ማዳበሪያ ዝውውሮችን ለመግታት የባለ ድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ እንደኾነም በመድረኩ ተነስቷል።
ጥብቅ ቁጥጥር እና ክትትል በማድረግ እንዲሁም መመሪያዎችን በአግባቡ በመተግበር ምርታማነትን ማሳደግ አንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ በግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን የደሴ ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ብርሃኔ ገብሬ ናቸው።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮቸን ለመፍታት መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንደሚካሄዱም አብራርተዋል። በመድረኩ አዲስ የተዋወቁ መመሪያዎች ቀርበው ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ዘጋቢ:- ደምስ አረጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
