
ደብረ ታቦር: ታኅሣሥ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ ወዋ ማገራ ቀበሌ የተፈጥሮ ሃብት ልማት በንቅናቄ ተጀምሯል።
የተፈጥሮ ሃብት ሥራ እየሠሩ ያገኘናቸው አርሶ አደር የቆዬ አደማሱ የተፋሰስ ሥራ ምርት እና ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ማኅበረሰቡ አካባቢውን አረንጓዴ ለማድረግ እየጣረ መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የወዋ ማገራ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ፋሲካ አስማረ ናቸው። አርሶ አደሮች ለተፈጥሮ ሃብት ሥራ እንክብካቤ ያለቸው ግንዛቤ እያደገ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
ከተፈጥሮ ሃብት ሥራ በተጨማሪ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በተሻለ ለመፈጸም እየተሠራ እንዳለ የተናገሩት ደግሞ የፋርጣ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማድነው ብርሃን ናቸው።
ከበፊቱ በተሻለ መንገድ የተፋሰስ ሥራን በተቀናጀ መልኩ ለመፈጸም እና ዘላቂ ልማት ለማምጣት አርሶ አደሮች እና ባለሙያዎች በጥምረት መሥራት አለባቸው ነው ያሉት።
“የተፈጥሮ ሃብትን መንከባከብ የህልውና ጉዳይ” መኾኑን የገለጹት ደግም የፋርጣ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ይርጋ ጌትነት ናቸው። የወረዳው አርሶ አደሮች የልማት እና የሰላም አርበኛ ናቸው ይህንን ተግባራቸውን በዚህ ዓመትም አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ የሺጥላ ፈቃዴ በዞኑ የበጋ ወራት የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በመከናወን ላይ መኾኑን ገልጸዋል።
እንደ ዞን በ14 የገጠር ወረዳዎች እና በ334 ቀበሌወች የተፈጥሮ ሃብት ሥራው እንደሚከናወን ተናግረዋል። በ1 ሺህ 23 ተፋሰሶች ላይ ከ59 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ መሬት የበጋ ወራት የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራው እንደሚለማም ገልጸዋል።
የማሳ እና የጋራ ላይ እርከን፣ የውኃ ማፋሰሻ እና መቀልበሻ ቦዮች እንዲሁም የተለያዩ የውኃ ማስረጊያ ስትራክቸሮች ከሚተገበሩ ተግባራት ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
