የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታን የሚደግፍ ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ ዘመቻ ሊካሄድ ነው።

187

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን የሚደግፍ ዓለም አቀፍ ዘመቻ ሊያካሂዱ መሆኑ ታውቋል።

የድጋፍ ንቅናቄው የተዘጋጀው የተባበሩት ኢትዮጵያውያን ለሰላምና ለእርቅ የተሰኘ ሲቪክ ማኅበር ከዓለም አቀፉ የእውቀት ልውውጥ መረብ ጋር በጋራ እንደሆነ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የዓለም አቀፍ ንቅናቄው ዓላማዎችም ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ስለ ሦስትዮሽ የድርድር ሂደቱ እውነታዎችን ለዓለም አቀፉ የማኅበረሰብ አባላት ማስገንዘብ እና ግንባታውን ለማጠናቀቅ የሚያግዝ የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰብ እንደሆኑ ነው የተገለጸው።

ዝግጅቱን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎች ጊዜው ሲደርስ ይፋ እንደሚደረጉም አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

በተያያዘ መረጃ በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲም ” ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ልማት እና ኢኮኖሚያዊ ውህደት” በሚል መሪ ሀሳብ ነገ በቪዲዮ የታገዘ ውይይት እንደሚያዘጋጅ አስታውቋል። ኤምባሲው ከሰሞኑ ባዘጋጀው ተመሳሳይ ይዘት ያለው ውይይት ኬንያውያን ምሁራን፣ የቀጣናዊ ውህደትና ልማት ተንታኞች እና የሀገሪቱ የቀድሞ ከፍተኛ መሪዎች የሕዳሴ ግድቡ ለቀጣናው ልማትና ትሥሥር ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌላቸው፣ ኢትዮጵያም ሀብቷን ለመጠቀም የማንንም ፈቃድ እንደማትጠብቅና የቀጣናው ሀገራት እንደሚደግፏትም ነው ምሁራኑ፣ የቀጣናዊ ውህደትና ልማት ተንታኞች እና የቀድሞ ባለሥልጣናት ያረጋገጡት።

በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና የኢትዮጵያ በሀብቷ የመጠቀም መብት ላይ የሚያካሂዱት ውይይትም ነገ ሰኔ 18/2012 ዓ.ም እንደሚጀምር የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በአስማማው በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleበአማራ ክልል ባለፉት 24 ሰዓታት የኮሮናቫይረስ የናሙና ምርመራ የተደረገላቸው ሁሉም ከቫይረሱ ነጻ ሆነዋል፡፡
Next articleመለስተኛ የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካዎችን በሁሉም ክልሎች ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ገለጹ፡፡