“የአጣዬ እና የሰንበቴ ከተማ ሕዝቦች ለሌሎች አጎራባች አካባቢዎች ተሞክሮ የሚኾን ተግባር እየሠሩ ነው” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)

12
ከሚሴ: ታኅሣሥ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን የአጣዬ ከተማ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰንበቴ ከተማ አሥተዳደር የአጎራባች ሕዝቦች የጋራ የሰላም እና የልማት መድረክ በሰንበቴ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) እና ሌሎች የክልል እና የዞን የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የአጎራባች ከተሞች ነዋሪዎች የሰንበቴ እና የአጣዬ ሕዝብ የተዋለደ እና የተጋመደ መኾኑን ገልጸዋል። አሁን ላይ አንድነታቸውን ጠብቀው በሰላም እየኖሩ መኾኑንም ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት የሁለቱን ሕዝቦች አንድነት ለመሸርሸር በርካታ ሙከራዎች ሲደረጉ የነበረ መኾኑን ነዋሪዎቹ አስታውሰዋል። ሕዝቦቹ ተባብረው አንድነታቸውን በማስጠበቃቸው አሁን ላይ ወንድማማችነታቸውን እያስቀጠሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
አሁን ላይ በጋራ የሰላም እና የልማት ተግባራትን እያከናወኑ መኾኑን ገልጸው በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስረድተዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ አለማየሁ ከዚህ ቀደም ቀጣናውን የግጭት ማዕከል ለማድረግ የጥፋት ኃይሎች ሢሠሩ ነበር ብለዋል።
መሪዎች እና ሕዝቦች በጋራ በሠሩት ተግባር በቀጣናው የተረጋጋ ሰላም መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት። አሁን ላይ ሁለቱ ከተሞች ወንድማማችነትን በማጎልበት በጋራ መገበያየት እና በጋራ የልማት ተግባራትን እያከናወኑ እንደሚገኙም አንስተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) “የአጣዬ እና የሰንበቴ ከተሞች ወንድማማችነት ለሌሎች አጎራባች አካባቢዎች ተሞክሮ የሚኾን ተግባር እየሠሩ ይገኛል” ብለዋል።
የሃይማኖት መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች በሠሩት የተቀናጀ ተግባር ቀጣናው አብሮነት የነገሰበት መኾኑን አረጋግጠናልም ነው ያሉት።
ሕዝቦቹ አሁን ላይ ከሰላም አጀንዳ ባሻገር በጋራ የልማት ሥራዎችን እየከወኑ መኾኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል። ይህን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።
በሕዝቦች ዘንድ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን ለመቅረፍም የክልሉ መንግሥት በትኩረት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም የሥራ ኀላፊዎቹ በሰንበቴ ከተማ እየተሠሩ ያሉ የልማት ተግባራትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleማስታወቂያ
Next articleየቅጥር ማስታወቂያ