መለስተኛ የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካዎችን በሁሉም ክልሎች ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ገለጹ፡፡

600

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 18/2012 ዓ.ም (አብመድ) በቀን እስከ 2 ሚሊዮን ዳቦ በማምረት የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የዳቦ ፍላጎት እንደሚያሟላ የታመነበት ፋብሪካ ዛሬ ተመርቋል፡፡

ሸገር ዳቦ ፋብሪካ በአቃቂ ክፍለ ከተማ በ43 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ነው የተገነባው፡፡ ለሥራውም 900 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ተገልጧል፡፡ ግንባታውን ከ4 እስከ 6 ወራት ለማጠናቅ ታቅዶ ነበር፤ የተጠናቀቀው ግን በ13 ወራት እንደሆነ ታውቋል፡፡ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ 100 ግራም ዳቦ በ 0.75 ሳንቲም ለሕዝቡ እንደሚያቀርብ ተገልጧል፡፡

በምረቃ መርሀ ግበሩ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶክተር)፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ (ኢንጂነር) እና የሚድሮክ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብነት ገብረ መስቀል ተገኝተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት ሁሉንም ከውጭ ሀገራት በማስገባት አሁን ያለውን የሕዝብ ቁጥር መቀለብ ስለማይቻል ሥራው በሀገር ውስጥ የማምረትና ራስን የመቻል ጅማሮ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ የዳቦ ፋብሪካው ሥራ መጀመር በአነስተኛ ዋጋ የአቅመ ደካሞችን ችግር ለመፍታት መንገድ የሚጠርግ እንደሆነም ዶክተር ዐብይ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ሁለት ዓመታትም ስንዴን ከውጭ ማስገባትን ለማቆም እየተሠራ መሆኑንና ለዚህ ደግሞ ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ መግባት ላይ መንግሥት በሰፊው ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ መለስተኛ የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካዎችን በሁሉም ክልሎች ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ዶክተር ዐብይ ገልጸዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ (ኢንጂነር) በበኩላቸው የዳቦ ፋብሪካው የአዲስ አበባ እናቶችና ሌሎች ነዋሪዎችን የዳቦ፣ የዘይት፣ የታክሲና ሌሎች ሰልፎችን የሚያስቀር የሥራ ጅማሮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ካሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ እንደሆነ የተገለጸው ፋብሪካው የሜድሮክ ኢትዮጵያ “ግሩፕ” አባል በሆነው “ሆራይዘን ፕላንቴሽን” ኩባንያ ነው የተገነባው። የሚድሮክ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብነት ገብረ መስቀል ደግሞ ፋብሪካው 120 ሺህ ኩንታል ስንዴ ማከማቻ ጎተራ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከሰው ንክኪ ነጻ ዘመናዊ ማሽኖች የተገጠሙለትና በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ፣ በሦስት ፈረቃዎች ደግሞ በቀን 2 ሚሊዮን የሚደርስ ዳቦ እንደሚያመርት አስታውቀዋል፡፡

ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ለ3 ሺህ ወጣቶች የሥራ እድል እንደፈጠረም ተገልጧል፡፡

ዘጋቢ፡- ጋሻው ፋንታሁን

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleየታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታን የሚደግፍ ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ ዘመቻ ሊካሄድ ነው።
Next articleየኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚገኙ ከ80 በመቶ በላይ ሆቴሎች በአብዛኛው ሥራ ማቆማቸውን መንግሥት አስታወቀ፡፡