
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ባንክ ከወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ጋር ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት በወጋገን ካፒታል ዋና መሥሪያ ቤት ተፈራርመዋል፡፡
ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ የአማራ ባንክ አ.ማ. በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ላይ የሰነደ መዋዕለ ንዋዮች ምዝገባ ለማካሄድ የሚያስችለውን ረቂቅ ሰነድ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ለባለሥልጣኑ አስረክቧል።
ስምምነቱን የፈረሙት የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮሐንስ አያሌው (ዶ.ር) እና የወጋገን ካፒታል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብሩታዊት ዳዊት ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የሕዝብ አክሲዮን ኩባንያዎች የመመዝገብ ግዴታ ባስቀመጠው መመሪያ መሰረት አማራ ባንክ በባለአክሲዮኖቹ የተያዙትን ሰነደ መዋዕለ ነዋዮች በተቀመጠው መስፈርት መሰረት የማስመዝገብ ሂደቱን የደንበኛ ሳቢ መግለጫ ማዘጋጀትን ጨምሮ እንዲያስተባብር እና ሌሎች ከካፒታል ገበያ ጋር የተያያዙ የማማከር ሥራዎችን እንዲሠራ ኀላፊነቱን ለወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ሰጥቶ ነበር።
የአማራ ባንክ አመራሮች ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ በባለሥልጣኑ በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ለማስመዝገብ ያሳዩትን ቁርጠኝነት በስምምነት ፊርማው ወቅት የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮሐንስ አያሌው (ዶ.ር) አመስግነዋል፡፡
በሀገራችን የተማከለ፣ በሕግ እና በተቋም የሚመራ የአክሲዮን ገበያ ባልነበረበት ጊዜ ከ164 ሺህ በላይ ባለአክሲዮኖችን እምነት በማግኘት የባንኩን አክሲዮኖች ለመሸጥ የቻለ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ዘመናዊ እና የተማከለ የካፒታል ገበያ ማቋቋም የመጡ ተጨማሪ እድሎችንን ለመጠቀም እና አማራ ባንክን በኢትዮጵያ እያደገ ባለው የካፒታል ገበያ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ላይ የባንኩን አክሲዮኖችን እንዲሸጥ ለማስችል፣ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ለማቋቋም፣ ተጨማሪ ካፒታል ማሰባሰብ የመሳሰሉ ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁለቱ ተቋማት የተፈራረሙት ስምምነት ወሳኝ እርምጃ መኾኑንም ዶክተር ዮሐንስ ገልጸዋል።
ስምምነቱ አማራ ባንክን ከቀዳሚ የፋይናንስ ተቋማት አንዱ ለመኾን በሚያደርገው ጉዞ ላይ ጤናማ አሥተዳደርን እና የገበያ ዲሲፕሊን መርሆችን ለማክበር ያለንን ትጋት የምናሳይበት ነውም ብለዋል።
ወጋገን ካፒታልም ለካፒታል ገበያው ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽዖ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ወጋገን ካፒታል የተለያዩ ዘርፎች ላይ ከሚሠሩ ኩባንያዎች ጋር በትብብር እየሠራ የሚገኝ ነው ተብሏል።
ይህም ኢንቨስትመንት ባንኩ በኢትዮጵያ የፋይናንስ እና ገበያዎች ልማት ውስጥ ያለውን ሚና እንደሚያጠናክርለት አመላካች ነው ሲሉ የኢንቨስትመንት ባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩታዊት ዳዊት ተናግረዋል፡፡
ወጋገን ካፒታል በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ የፋይናንስ ዘርፉን ለመደገፍ ያስችል ዘንድ ደንበኞቹን በእያንዳንዱ እርምጃ ለመርዳት ዝግጁ መኾኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አያይዘው ገልጸዋል፡፡
አማራ ባንክ በሀገሪቱ የካፒታል ገበያ ውስጥ ለሚኖረው ሚና እና ተሳትፎ ወጋገን ካፒታል ላይ ለጣለው ኀላፊነት እና እምነት ወጋገን ካፒታል ለመወጣት ይሠራል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
