ሁሉም ጤና ጣቢያዎች አምቡላንስ እንዲኖራቸው ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።

12
ወልድያ: ታኅሣሥ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ገስጥ ጥላሁን በክልሉ ያሉ ሆስፒታሎች ሁሉም አምቡላንስ እንዲኖራቸው መደረጉን ገልጸዋል።
በሂደት ሁሉም ጤና ጣቢያዎች አምቡላንስ እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት። ቢሮው በራሱ አቅም እና ከጤና ሚኒስቴር በሚያገኘው ድጋፍ በየጊዜው ለሁሉም ዞኖች አምቡላንስ እያደረሰ መኾኑን የገለፁት ምክትል ኀላፊው ዞኖች እና ወረዳዎች ኅብረተሰቡን በማስተባበር የአምቡላንስ ጉድለትን ለመሸፈን እየተሠራ መኾኑንም አስረድተዋል።
በዚህ ዓመት 28 አምቡላንሶች ለሁሉም ዞኖች ተሰራጭቷል። ለሰሜን ወሎ ዞን የተመደቡ ሁለት አምቡላንሶችንም አስረክበናል ነው ያሉት።
ለዞኑ የተመደቡ አምቡላንሶችን የተረከቡት የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ሲስተር ፈለቁ መኮንን እንደ ዞን በግንባታ ላይ ያሉ ሁለት ሆስፒታሎችን ጨምሮ ሰባት ሆስፒታሎች እና 68 ጤና ጣቢያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
አምስቱ ሆስፒታሎች የራሳቸው አምቡላንስ እንዳላቸው ገልጸው አዲስ የተመደቡት አምቡላንሶች በዚህ ዓመት ግንባታው ለሚጠናቀቀው የዓይና ቡግና ሆስፒታል ሥራ ማስጀመሪያ እንደሚኾኑ ነው የገለጹት።
ከጤና ጣቢያ አኳያ በስታንዳርዱ መሠረት አምቡላንስ ያላቸው ከ40 በታች ናቸው ያሉት ሲስተር ፈለቁ እያንዳንዱ ጤና ጣቢያ አምቡላንስ እንዲኖረው ለማድረግ ተጨማሪ 28 አምቡላንሶች ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የሰሜን ወሎ ዞን መልከዓ ምድር ለመደበኛ ተሽከርካሪ ምቹ ባለመኾኑ እናቶች ወደ ጤና ተቋም በቀላሉ ሊደርሱ የሚችሉት በአምቡላንስ በመኾኑ ሊሟላ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አምቡላንሶች የሕዝብ ሀብት በመኾናቸው አጠቃቀሙን መንግሥት ብቻ ሳይኾን ኅብረተሰቡም ሊከታተል እና ሊቆጣጠር እንደሚገባ ሲስተር ፈለቁ ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article‎ሰላም የማይፈልጉ አካላት የሚያደርሱትን ፈተና በመገንዘብ ለሰላም መሥራት ይገባል።
Next articleአማራ ባንክ እና ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ምዝገባን በተመለከተ አብሮ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።