
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን የሰላምን ጥሪ ተቀብለው የገቡ የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለመቀላቀል እና ለማቋቋም ከማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር በባሕር ዳር ከተማ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሰላምን ጥሪ ተቀብለው የገቡ የቀድሞ ተዋጊዎች እና ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አካላት እየተሳተፉ ነው።
በብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን የመልሶ ማቋቋም ዳይሬክተር ገመዳ ዓለሜ የመድረኩ ዓላማ በሀገራችን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የአማራ ክልል የቀድሞ ተዋጊዎች የመልሶ ማቋቋም አፈጻጸም እና ቀጣይ የሥራ ትኩረት በማየት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ለማድረግ ነው ብለዋል።
ጦርነት በዜጎች ላይ ዘርፈ ብዙ ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥፋት የሚያደርስ እንደኾነ ገልጸዋል። ሰላም የሁሉም ነገር ዋስትና ነው፤ ሠርቶ የመለወጥ፣ ወልዶ የማሳደግ፣ ወጥቶ የመግባት እና ዘርቶ የማፍራት መሠረት መኾኑንም አንስተዋል።
ሰላም የሀገር ህልውና መሠረት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ የሀገራችን ሰላም የማይፈልጉ አካላት በየጊዜው የሚያደርሱትን ፈተና በመገንዘብ ለሰላም መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
በየአካባቢው እያጋጠመ ላለው የጦርነት ጥፋት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የጦርነትን መዘዝ እና የሰላምን ትሩፋት በአግባቡ በመገንዘብ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
