“ሕዝብ ሰላምን ይፈልጋል፣ ሰላምን የማይፈልገው በግጭት ተጠቃሚ የኾነ ብቻ ነው” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)

2
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምዕራብ ጎጃም ዞን ከቡሬ ከተማ እና ከቡሬ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ የችግሮችን መነሻ በውል በመረዳት የጋራ መፍትሔ ማስቀመጥ ያስፈልጋል ብለዋል። ችግሮቻችንን እኛው ውስጥ ስላሉ መፍትሔውም እኛው ጋር ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ቡድን ሀገርን ለጠላት አሳልፎ የሚሰጥ፣ ለሕዝብ እና ለሀገር የማይጠቅም መኾኑን ተናግረዋል። በሀሰተኛ ማደናገሪያ ተነስቶ ሕዝብን እያጎሳቆለ መኾኑንም ገልጸዋል።
ልጆቻችሁ እንዳይማሩ የሚያደርገውን፣ በደስታ እና በሀዘን እንዳትገናኙ የሚያደርጋችሁን ማውገዝ ይጠበቅባችኋል ነው ያሉት። ሕዝብ ከዚህ በላይ እንዲሰቃይ መፍቀድ እንደማይገባም ተናግረዋል።
ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር በጋራ በመሥራት ሰላማቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
የትጥቅ ትግል ሕዝብን እና ሀገርን አይጠቅምም፤ ይልቅስ ወደኋላ እያስቀረ ነው ብለዋል። አብሮ የኖረን ማኅበረሰብ ለማነጣጠል የሚሠሩ ሴረኞችን መታገል እንደሚገባም ተናግረዋል።
በየአካባቢው ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን እየመከሩ የሰላም አማራጭን እንዲጠቀሙ ማድረግ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለሰላም መረጋገጥ እንዲሠሩም ጠይቀዋል።
የሕዝብ ተቆርቋሪ መስለው ሀሰተኛ መረጃዎችን እያራገቡ ግጭት ለሚያባብሱ ኃይሎች ጀሮ መስጠት እንደማይገባም ተናግረዋል። ሰላምን በማረጋገጥ የቡሬ ወለጋን መንገድ መጨረስ እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ አመላክተዋል።
በአንድነት የአካባቢያቸውን ሰላም እንዲጠብቁም አሳስበዋል። እስካሁን ከጠፋው ጥፋት መማር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) በውይይታችን ሕዝብ ሰላምን መምረጡን እና ለሰላም መነሳቱን ተረድተናል ነው ያሉት።
ቡሬ እና አካባቢው የኢንዱስትሪ ማዕከል ነው ያሉት አሥተባባሪው ባለፉት ዓመታት ግን ባላት ጸጋ ልክ ሳትጠቀም ቆይቷል፤ በአጭር ጊዜ ሰላምን በማረጋገጥ ወደ ኢንዱስትሪ ማዕከልነቱ መመለስ ያስፈልጋል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የአማራ ክልልን ሕዝብ በብዙ መልኩ ማጎሳቆሉን ተናግረዋል። የመንግሥት ፍላጎት ሰላም እንዲረጋገጥ፣ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር፣ ተማሪዎች እንዲማሩ እና እናቶች በጤና ተቋማት እንዲታከሙ ነው ብለዋል። ጽንፈኛው ግን ተማሪዎች እንዳይማሩ፣ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖር እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
ጽንፈኛው ቡድን ንጹሐንን ያግታል፣ ይዘርፋል፣ ይቀማል ያንገላታል ነው ያሉት። በፍጥነት ሰላምን ማረጋገጥ ካልተቻለ ችግሩ በእያንዳንዱ ቤት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ሕዝብ በጽንፈኛው ቡድን እኩይ ተግባር መማረሩንም ገልጸዋል። ጽንፈኛው ቡድን ጨካኝ እና ዘራፊ ቡድን መኾኑንም አመላክተዋል።
ሕዝብ በራሱ አቅም ሰላምን ማረጋገጥ ይችላል ያሉት አሥተባባሪው ሕዝብ በራሱ ሰላምን የማረጋገጥ አቅም አለው፤ በሌሎች አካባቢዎች ሕዝብ እየመከረ እና እየታገለ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ እያደረገ ነው፤ እናንተም ይሄን ማድረግ አለባችሁ ነው ያሉት። “ሕዝብ ሰላምን ይፈልጋል፣ ሰላምን የማይፈልገው በግጭት ተጠቃሚ የኾነ ብቻ ነው” ብለዋል።
ጽንፈኛው ቡድን የሚያስመልሰው የሕዝብ ጥያቄ እንደሌለም ተናግረዋል። መንግሥት ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት እንዲኖር እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በየአካባቢያቸው ያለውን ጽንፈኛ ቡድን እየመከሩ እንዲመልሱም አሳስበዋል። ሰላም በአንድ ወገን ብቻ አይመለስም፤ የጋራ ሥራ እና ቅንጅት ይጠይቃል ነው ያሉት።
የእኛ ፍላጎት ሰላምን ማረጋገጥ ነው፤ ሕዝብም ሰላምን ይፈልጋል፤ በቅንጅት የተጀመረውን ሰላም ዘላቂ ማድረግ ያስፈልገናል ብለዋል።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ሰላም የሐቀኞች ውጤት ናት” አቶ ፍስሃ ደሳለኝ