“ሰላም የሐቀኞች ውጤት ናት” አቶ ፍስሃ ደሳለኝ

1
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የዞን ከፍተኛ መሪዎች ዘካሪ፣ መካሪ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ለዘላቂ ሰላም እና ልማት በሚል መሪ መልዕክት በሰሜን ወሎ ዞን ጉባላፍቶ ወረዳ ከሀገር ሽማግልዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ ለሰላም ብለው ዋጋ የከፈሉ ወንድም እና እህቶቻችንን በማሰብ እና እውነት ላይ በመቆም ስለሰላም እውነትን መነጋገር ይገባል ብለዋል።
ለሕዝብ ሰላም እና ለሀገር አንድነት የቆሙ፣ ለዚህም ብለው መስዕዋትነት የከፈሉ በርካታ የሰሜን ወሎ የሕዝብ ልጆች መኖራቸውንም ገልጸዋል። መገዳደል ይበቃል፣ ከዚህ በኋላ ሰክኖ መወያየት እና ሰላምን መምረጥ ይገባል ነው ያሉት።
ታጣቂዎች ሰላምን ሲመርጡ ለሕዝብ ይበጃሉና ወንድሞቻችን ናቸው፤ በጥፋት ከቀጠሉ ግን ለሕዝብ ሲባል በጋራ ታግለን ልናስተካክላቸው የሚገቡ ጠላቶች ናቸው ብለዋል አቶ ፍስሃ። ከዚህ በኋላ ዝምታ አይበጅም፤ እውነቱን ተነጋግሮ ለመፍትሔው በጋራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
የሰሜን ወሎ አካባቢ የጦርነትን ውጣ ውረድ አይቶታል፤ በጦርነት የሚፈታ ጥያቄ እንደሌለም አያጣውም፤ ስለዚህ አስታራቂ አባቶች ይውጡና የታጠቁ ልጆችን መክረው ወደ ሰላም ያስገቡ ብለዋል።
“ሰላም የሐቀኞች ውጤት ናት፤ በሐቀኝነት ላይ መቆም እና አጥፊን በልኩ ገስጾ ለይቅርታ፣ እርቅ እና ሰላም ማዘጋጀት ያስፈልጋል” ሲሉም ተናግረዋል። ይህ ሲኾን ሰላም ይሰፍናል፣ ሕዝብም እፎይታ አግኝቶ በሙሉ አቅሙ እያለማ ይኖራል ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የየአካባቢዎች ታጣቂዎችን አካሄድ ስህተት መኾኑን
በውል ተገንዝበው ይምከሩ፤ መንግሥት ደግሞ ወደ ሰላም የሚመጡትን እየተቀበለ እና እየደገፈ በሰላም እንዲኖሩ ያመቻቻል ነው ያሉት አቶ ፍስሃ።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር የሃይማኖት አባቶች የሚመሩት ሕዝብ እፎይታ እንዲያገኝ መፍትሔ መፈለግ፣ እርቅ እእንዲወርድም መሥራት አለባቸው ብለዋል።
የሰፈሩን ሰዎች እዋጋላችኋለሁ እያለ የሚሸነግል እና ሕዝብን የሚዘርፍ ታጣቂ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕግ ሊያስከብር ወደቀየው በሚሄድ ጊዜ ልብሱን ቀይሮ የሚደበቀው በሕዝቡ ውስጥ ነው ብለዋል።
ሰላምን የፈለገ ሕዝብ እንዲህ አይነቱን ተግባር በፍጥነት ለማስቆም መተባበር እንዳለበትም አሳስበዋል። ለሕዝብ የሚቆረቆር ሁሉ ለእውነት መቆም፣ እውነትን መናገር፣ ጥፋተኛን ለይቶ ማወቅ እና ለሕግ አሳልፎ መስጠትም አለበት ነው ያሉት።
የሕዝብን ሰላም ለማስጠበቅ መስዕዋትነት ጭምር እየከፈለ የሚያገለግልን የጸጥታ መዋቅር መደገፍ እና በትብብር መሥራት ይገባልም ብለዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች እውነትን መርምረው በማወቅ እና አጥፊን በመምከር ለሰላም ቁልፍ ሚናቸውን እንዲወጡም ዋና አሥተዳዳሪው ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleለእውነት እና ለሰላም በቁርጠኝነት እንነሳ፣ ለሰላም የሚከፈለውን ዋጋ እንክፈል።
Next article“ሕዝብ ሰላምን ይፈልጋል፣ ሰላምን የማይፈልገው በግጭት ተጠቃሚ የኾነ ብቻ ነው” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)