“ታጣቂዎች ወንድሞችና ወዳጆች ሊኾኑን የሚችሉት ከጥፋት ሲወጡ ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ

2
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የዞን ከፍተኛ መሪዎች ዘካሪ፣ መካሪ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ለዘላቂ ሰላም እና ልማት በሚል መሪ መልዕክት በሰሜን ወሎ ዞን ጉባላፍቶ ወረዳ ተወያይተዋል።
የሀገር ሽማግልዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ተወካዮች በውይይቱ ተሳትፈዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ከአማራ ሕዝብ እና ከኢትዮጵያም ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተቆራኝቶ የሕዝብ ጥቅም ለመሸጥ የሚደራደርን አካል በስሙ እና በግብሩ እየጠሩ ጥፋቱን በሀቅ መነጋገር እና ከድርጊቱ እንዲቆጠብ በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል።
ታጣቂዎች የኛ ልጆች፣ ወንድሞች እና ወዳጆች ሊኾኑ የሚችሉት በሰላም ገብተው ለሕዝብ እና ለሀገር ልማት ሲሠሩ፣ ራሳቸውንም ሲጠቅሙ ነው ብለዋል። ጫካ ለጫካ እየተሹለከለኩ በበደል ላይ በደል ሲፈጽሙ እና ሕዝብን እየበደሉ መቆየት በሚፈልጉት ላይ ግን ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ እንደሚተገበር አስገንዝበዋል።
መገዳደል ይበቃል፣ ሽፍትነት ኋላቀርነት ነው፤ ከዚህ በላይ ከተራዘመ በወጉ መደሰትም ኾነ ሀዘንን መካፈል አይገኝም ነው ያሉት። የግጭት ጫናው መጀመሪያ ላይ የሚያርፈው በሕዝብ ላይ ነውና ይህንን ተገንዝቦ ሁሉም ለሰላም መሥራት ይገባል ብለዋል።
መንግሥት በግጭት ውስጥም ኾኖ ለሕዝብ የሚጠቅሙ ልማቶችን ያለፋታ እየሠራ ስለመኾኑም አንስተዋል። ታጣቂዎች ደግሞ ከሕዝብ ልማት በተቃራኒ ቆመው እና ከውጭ ጠላቶች ጋር ተባብረው ሕዝብን እያሳዘኑ መኾኑን አቶ ይርጋ አብራርተዋል።
የሕዝብን ጥቅም አሳልፈው ለመስጠትም ከጠላት ጋር የሚፈራረሙ የሀገር ጠላቶች ኾነው ተገኝተዋል ነው ያሉት።
የመንግሥት አቋም ሀገራዊ አንድነትን ጠብቆ፣ ሰላምንም አስፍኖ ሀገር እና ሕዝብን ማልማት ነው ብለዋል። ሕዝቡም ይህንን በመረዳት ከሰላም እና ከልማቱ ጎን ይቁም ብለዋል።
ሕግ ይከበራል፤ ማኅበረሰቡ ከመንግሥት የጸጥታ አባላት ጎን እየቆመ ማገዝ፣ በውስጡ ተሰግስገው ለስቃይ የሚዳርጉትን ታጣቂዎችንም የሚሰሙትን ይምከር፤ አሻፈረኝ የሚሉትን ደግሞ ለራሱም ደኅንነት ሲል አሳልፎ ይስጥ ነው ያሉት።
የመንግሥት የምንጊዜም ምርጫ ሰላም ነው፤ ለሰላም የሚገባ ከኾነ በክብር ለመቀበልም ዝግጁ ነን ብለዋል።
የጉባ ላፍቶ ወረዳ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እንደሌሎች አካባቢዎች ሁሉ ለሰላም እንዲመክሩ እና እንዲዘክሩም አቶ ይርጋ አሳስበዋል።
ለሕዝብ ሰላም ሲሉ መስዕዋትነት የሚከፍሉ የመንግሥት አመራሮች እና የጸጥታ አካላት እንዳሉት ጠቅሰዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎችም ለሕዝባቸው ሲሉ በሀቅ ላይ የተመሰረተ ንግግር ማድረግ እና ለእርቀ ሰላም መሸምገል አለባቸው ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራር ሜጀር ጄኔራል አድማሱ ዓለሙ የጦርነት አሸናፊ እና ተሸናፊ የለውም፤ የጦርነት መጨረሻው ድርድር ነው ብለዋል። ጦርነት እና ግጭት ምክንያት አልባ እና በመዝረፍ ኢኮኖሚ ለማካበት ያለመ ከኾነ ግን ይራዘማል ነው ያሉት።
አሁን እንደሀገር የገጠሙን ታጣቂዎችም የሕዝብን ጥያቄ በማስመለስ ሰበብ ሀብት ለማካበት የሚጥሩ ናቸው ብለዋል።
ሰላምን የሚፈልግ ሁሉ ችግሮችን እና የሚፈጸሙ ግፎችን በግልጽ መነጋገር እንዳለበትም አስገንዝበዋል። ሕዝብም ለራሱ ሰላም እና ለሀገር ደህንነት ሲል ከሠራዊቱ ጎን መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።
የሀገር መከላከያ ተልዕኮ ሕዝብ እና ሀገርን መጠበቅ ነው ያሉት ጄኔራሉ የታጠቀ ኀይል መሣሪያውን አስቀምጦ ወደ ሰላም መምጣት እና ማልማት እንዲችል ሌት ተቀን እየሠራን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሰላምን የሚፈልግ የታጣቂ አባል ካለ ያለምንም ቂም በቀል በክብር ለመቀበል ዝግጁ ነን ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleበሸዋ ሮቢት ከተማ አንጻራዊ ሰላም ተፈጥሯል።
Next articleለእውነት እና ለሰላም በቁርጠኝነት እንነሳ፣ ለሰላም የሚከፈለውን ዋጋ እንክፈል።