
ወልድያ: ታኅሣሥ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት “የመደመር መንግሥት እይታ የዘርፎች እምርታ” በሚል መሪ መልዕክት ለአባል የመንግሥት ሠራተኞች ሥልጠና እየሰጠ ነው።
የከተማ አሥተዳደሩ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ አስናቀች ኃይሌ አባላቱ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ በተሰማሩበት መስክ ስኬት የማስመዝገብ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ያደገች ሀገር እና ከተማ ለትውልድ ለማሻገር መንግሥት እና ፓርቲ የጣለባቸውን ኀላፊነት በአግባቡ እንዲወጡም ኀላፊዋ ገልጸዋል።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋዬ ገብሬ ለፓርቲው ስትራቴጂክ እቅድ ስኬት የ2018 እቅድ አፈጻጸም ጉልህ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።
አባል የመንግሥት ሠራተኞች የፓርቲውን ርዕይ በአግባቡ ተረድተው የስኬት ጉዞን ለማሳለጥ ይቻል ዘንድ ሥልጠናው አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የመንግሥት እና የፓርቲ ርእይ ተቀብሎ እና ከልብ ተግባብቶ ቀን ከሌት መሥራት ርእዩን ለማሳካት እና ለኢትዮጵያ ብልጽግና ወሳኝ መኾኑንም ነው የተናገሩት።
አምነን በፓርቲ ጥላ እስካለን ድረስ መሪዎችን እየተካን ርእይን ለማስቀጠል በቁርጠኝነት መሥራት የሚያስችል ቁመና መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል። ለዚህም “ችግሮችን የሚሸከም ትከሻ ያለው የፓርቲ አባል በመገንባት ፈተናን ተቋቁሞ ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ አስፈላጊ መኾኑን ነው” ያስረዱት።
ከመምሪያ እስከ ቀበሌ ያሉ የብልጽግና ፓርቲ አባል መንግሥት ሠራተኞች የሚሳተፉበት ሥልጠና ለሁለት ቀናት የሚቆይ መኾኑ ተመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
