
ደሴ: ታኅሣሥ 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተደረገው የምርጥ ዘር ድጋፍ በበረሃ አንበጣ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሦሥት ወረዳዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።
የሰልፍ ኸልፕ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ ተጋላጭ የኾኑ አርሶ አደሮች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የክትትል እና ግምገማ ባለሙያ ዋለልኝ ከበደ ድርጅቱ የግብርና ዘርፉን ለማገዝ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ደግሞ ለበጋ መስኖ ስንዴ ሥራ እንዲኾን የስንዴ ምርጥ ዘር ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል። ድርጅቱ ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት 435 ኩንታል ለበጋ መስኖ ስንዴ የሚውል ምርጥ ዘር ድጋፍ ማድረጉንም አንስተዋል።
በአማራ ክልል ለሚገኙ ሦሥት ወረዳዎች የምርጥ ዘር ስንዴ ድጋፉ እየደረሰ መኾኑንም አብራርተዋል። ወረባቦ፣ ራያ ቆቦ እና ባቲ ወረዳዎች የምርጥ ዘር ድጋፍ የተደረገላቸው ወረዳዎች ናቸው።
ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ 145 ኩንታል ለበጋ መስኖ ልማት የሚውል ምርጥ ዘር ለወረባቦ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት በዛሬው እለት ማስረከባቸውንም ነው የተናገሩት።
ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ግብዓት የሚኾን 290 ኩንታል ምርጥ ዘር ለራያ ቆቦ እና ለባቲ ወረዳዎች ርክክብ እየተደረገ መኾኑንም ነው የጠቆሙት።
የሥርዓተ ምግብን ለማሻሻል የሚያግዙ ሰባት አይነት የተመረጡ ዘጠኝ ኩንታል የጓሮ አትክልት ዘሮችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ መደረጉም ተመላክቷል። በቀጣይ ቀናትም 4 ነጥብ 5 ኩንታል በመስኖ የሚለማ የጓሮ አትክልት ዘር ለማሰራጨት ዝግጅት መደረጉንም አቶ ዋለልኝ አመላክተዋል።
የገጠር ቁጠባ እና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ለማጠናከር እና አርሶ አደሮች በገቢ ማስገኛ ሥራ እንዲሰማራ 37 ሚሊዮን ብር ከ1 ሺህ 700 በላይ ለሚኾኑ አርሶ አደሮች በተዘዋዋሪ ብድር መሰራጨቱንም ጠቅሰዋል ባለሙያው።
በሰልፍ ኸልፕ አፍሪካ ፕሮጀክት የወረባቦ ወረዳ ኦፊሰር ስማቸው ይበይን ከዚህ ቀደም 80 ኩንታል ምርጥ ዘር ለመኸር ሥራ ማሰራጨታቸውን አንስተው የተደረገው ድጋፍ የአርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በኩል የላቀ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
የአሁኑ ድጋፍም በበረሃ አንበጣ ጉዳት የደረሰባቸውን አርሶ አደሮች ችግር እንደሚያቃልል ነው የተናገሩት።
በርክክቡ ላይ የተገኙት የወረባቦ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብዱ አሊ በወረዳው 1 ሺህ 100 ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ለማምረት ማቀዳቸውን ገልጸዋል።
ሰልፍ ኸልፕ አፍሪካም የመስኖ ልማት ሥራውን ለመደገፍ ያደረገው የምርጥ ዘር ድጋፍ ለውጤታማነቱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመላክተዋል።
ድጋፉ የበጋ መስኖ ልማት ተጠቃሚ ለኾኑ አርሶ አደሮች እንደሚሰራጭም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ጀማል ይማም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
