“የሰላም ትሩፋትን ለማግኘት ስክነት እና መወያየት ያስፈልጋል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

3
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምዕራብ ጎጃም ዞን ከቡሬ ከተማ እና ከቡሬ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
በውይይቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ
የቡሬ ከተማ እና ወረዳው ከሌሎች ወረዳዎች በበለጠ ቅርበት የአርሶ አደሮችን መሠረታዊ ምርቶችን የሚያቀናብር፣ ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ግዙፍ የኢንድስትሪ ፓርክ፣ ትልቅ ሰብስቴሽን፣ የቡሬ-ወለጋ እና የቡሬ ሽንዲ የአስፋልት መንገድ ግምባታ እና የዓባይ ዳር ለዳሩ የማዕድን ሃብት ባለቤት ነው ብለዋል።
ነገር ግን ባለፉት ዓመታት የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የአካባቢው ሕዝብ ጸጋውን እንዳይጠቀም አድርጎታል ብለዋል። በትውልድ ላይ ክፍተት የሚፈጥር ችግር መፈጠሩንም ተናግረዋል።
ከአንጻራዊ ሰላም ወደ ተሟላ ሰላም ለመሸጋገር መመካከር እና መወያየት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
መተኳኮስ በቃኝ፤ ሰቆቃ በቃኝ፤ መጎሳቆል በቃኝ እና የልጆች አለመማር ይበቃል ማለት እንደሚገባ ተናግዋል።
የቡሬ እና አካባቢዋ ሕዝብ ሰላምን ያጽና፣ ለሀቅ እና ለእውነት ይቁም፤ አካባቢውንም ወደተሟላ ሰላም ይመልስ ብለዋል። አካባቢው ወደ አንጻራዊ ሰላም እንዲመለስ ላደረገው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ምስጋና አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የችግሩ መነሻ ምክንያቶችን መለየት እና መፍትሔ ማመላከት እንደሚገባ ተናግረዋል። ችግሮችን ሰከን ብሎ መፍታት፣ ታማኝ እና ታጋሽ በመኾን የጎደለውን መሙላት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የመንግሥት እና የሕዝብ ግንኙነት በመተማመን እና በስክነት ላይ የተመሠረተ ከኾነ ሰላም ይረጋገጣል፣ ልማትም ይመጣል ብለዋል። ስክነት እና መተማመን ከሌለ ግን የሰላም ትሩፋትን ማግኘት አይቻልም ነው ያሉት። “የሰላም ትሩፋትን ለማግኘት ስክነት እና መወያየት ያስፈልጋል” ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በስክነት ችግሮችንን መፍታት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
የጎጃምን ሰላም እና የሰላም እሴት ግንባታ ለመመለስ፣ መምከር እና መደማመጥ ያስፈልጋል ብለዋል። ባለፉት ዓመታት የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምስቅልቅል ማስከተሉን ተናግረዋል። የክልሉን ሕዝብ መጉዳቱን ገልጸዋል። የክልሉ ሕዝብ ባሕል፣ እሴት፣ ባሕል እና ወገን መጎዳቱን ነው የተናገሩት።
የትውልድ መቅረጫ የነበሩ የትምህርት ተቋማት ተዘግተው መኖራቸውን ነው የገለጹት። ከአማራ ክልል ሕዝብ ባሕል እና እሴት ያፈነገጠ አስነዋሪ ድርጊት መፈጠሩንም ተናግረዋል። የራስን ዕድል እና እጣ ፋንታ ለመወሰን በመወያየት ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ባለፉት ዓመታት እርቅ እና ሰላም ይምጣ ያሉ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች መዋረዳቸውን እና መገደላቸውንም ገልጸዋል። የክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት ንብረት መውደሙንም ተናግረዋል። ማኅበራዊ እንቅስቃሴ መገደቡንም ገልጸዋል። የአገልግሎት እና የምርት እንቅስቃሴ ከተገደበ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እድገትን ማረጋገጥ እንደማይቻል ነው የተናገሩት።
የክልሉ ሰብዓዊ ልማት ስብራት ገጥሞት እንደቆዬም አመላክተዋል። በሰብዓዊ ልማት ላይ የደረሰው ጉዳት ለቀጣይ ዓመታት ዳፋ ይዞ እንደሚመጣም አንስተዋል።
ሕዝቡም በሥነ ልቦና ጫና ውስጥ መቆየቱን ገልጸዋል። ከዚህ ችግር በፍጥነት ለመውጣት መወያየት እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ።
Next articleሰልፍ ኸልፕ አፍሪካን የተባለ መንግሥታዊ ያልኾነ ድርጅት ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ለበጋ መስኖ የሚኾን የምርጥ ዘር ድጋፍ አድርጓል።