
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 03/ 2018 ዓ.ም (አሚኮ) አካል ጉዳተኝነት በሰው ልጆች ላይ በማንኛውም ጊዜ ሊደርስ የሚችል ክስተት ነው። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት ፌዴሬሽን ባሳለፍነው ጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም ባወጣው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች ይገኛሉ።
የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌደሬሽን የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ ቁጥራቸው ከ4 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ አካል ጉዳተኞች በክልሉ ይገኛሉ፡፡
እነዚህ አካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋር እኩል በማኅበረሰቡ ውሰጥ ውጤታማ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው እና ተጠቃሚ እንዳይኾኑ የተዛቡ አመለካከቶች እና አካባቢያዊ መሰናክሎች ይገጥሟቸዋል።
ቁጥራቸው ዝቅተኛ ቢኾንም መሰናክሎችን አልፈው ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ አድርገው በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አበርክቶ ያላቸው ግን አልጠፋም።
የእንቅስቃሴ ውስንነት ያለበት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው ታደሰ አበረ አንዱ ነው። ታደሰ ለረጅም ጊዜ የጫማ ማጽዳት እና ማስዋብ ሥራ መሥራቱን ነግሮናል፡፡
በዚህ ሂደት ያጠራቀማት ገንዘብ ላይ ብድር ጨምሮ በ2015 ዓ.ም የእንቅስቃሴ ውስንነት ላለበት ሰው በሚያስቸግረው የሽመና ሥራ ላይ መሰማራቱን ነግሮናል።
ሦሥት የሸማ መሳሪያዎችን ገዝቶ ሌሎች ሰዎችን በመቅጠር የሽመና ሥራን አሀዱ እንዳለም ገልጾልናል። ከእግር እንቅስቃሴ ውጭ ያሉ የሸማ ሥራዎችን እየሠራ እንደኾነም ጠቅሶልናል።
አሁን ላይ ከራሱ አልፎ ለሌሎች 12 ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። የነበሩትን ሦሥት የሸማ መሳሪያዎች ወደ 12 ከፍ አድርጓል፡፡ ከሸማ ሥራ በተጨማሪ ለውዝ እና ቡናን አስፈጭቶ በማሸግ ለተገልጋዮች በመሸጥ ላይም ተሠማርቷል፡፡ እንደሱ አካል ጉዳት ላለበት ሰው ሥልጠና በመስጠት ከተቀጣሪነት ወጥቶ የራሱን ሥራ እንዲጀምር አድርጓል፡፡
አሁን ላይ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ክህሎት መምሪያ ባመቻቸለት የመሥሪያ ቦታ ሥራውን እየከወነ ይገኛል፡፡ የገብያ ትስስር፣ የተለያዩ ሥልጠናዎች እና ብድር ቢመቻችለት ደግሞ ከ100 እስከ 150 ለሚኾኑ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ እንዳለው ነግሮናል፡፡
ሌሎች አካል ጉዳተኞች የሌሎችን ሰዎች እጅ ከመጠበቅ ወጥተው የሚችሉትን ሥራ ሠርተዉ ራሳቸዉን ተጠቃሚ እንዲያደርጉም አስገንዝቧል።
የአማራ ክልል የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ፍሬሰላም ዘገየ አካል ጉዳተኞች በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካ ዘርፍ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ተናግሯል፡፡
ቁጥራቸው ጥቂት ቢኾንም ራሳቸውን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያደረጉ እና በአርያነት የሚጠቀሱ በአማራ ክልል የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ሁለት በመቶዎች ብቻ መኾናቸውንም ጠቅሰዋል። እነዚህ ወደ ኃላ እንዳይመለሱ ማበረታቻ የሚኾን እውቅና ከሥራ እና ክህሎት ቢሮ ጋር በመቀናጀት ተሠርቷል ብለዋል። በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ለሥራ ፈላጊዎች የሚዘጋጁ የመሥሪያ ቦታዎች አካል ጉዳተኞችን አካታች አለማድረጋቸው፣ የባንኮች የብድር አሰጣጥ ቅድመ ሁኔታዎች በኢኮኖሚ ዘርፉ ላይ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እንቅፋት ኹኗል ብለዋል፡፡
እንዲህ አይነት ክፍተቶች እንዲታረሙ እና አካል ጉዳተኞች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የአማራ ክልል አካል ገዳተኞች ፌደሬሽን የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
በመንግሥት መዋቅሩ እና በበጎ አድራጎት ተግባሮች ላይ የተሰማሩ ተቋማት ከአካል ጉዳተኞች ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት አኳያ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
