በምግብ ራስን ለመቻል የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርን በውጤታማነት መተግበር ያስፈልጋል።

6
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የእንስሳት ሃብት ልማት ለሌማት ቱርፋት ያለው አስተዋጽኦ ጤናማ ትውልድን ከመፍጠር ባለፈ የድህነት ቅነሳን እና የኢኮኖሚ እድገትን የሚያረጋግጥ ወሳኝ ዘርፍ ነው።
በእንስሳት ሃብት ልማት ከፍተኛ አቅም ካላቸው ከተሞች መካከል የደብረ ብርሃን ከተማ አንዷ ናት።
በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር እየተከናወኑ ስለሚገኙት የሌማት ትሩፋት እና የእንስሳት ሃብት ልማት ዙሪያ የከተማዋ ከንቲባ በድሉ ውብሸት ለአሚኮ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ተከትሎ ከተማ አሥተዳደሩ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል። በወተት ልማት፣ በሥጋ፣ በዶሮ እና በእንቁላል ልማት በሰፊው እየተሠራበት እንደኾነ ተናግረዋል።
አሁን እየተመረተ ያለውን የወተት ምርት በማሳደግ በቀን እስከ 150 ሺህ ሊትር ለገበያ ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል። ይህንን ለማሳካትም የተሻሻሉ ዝርያዎችን በመጠቀም፣ የግል ባለሃብቶችን በማበረታታት፣ በግለሰብ ደረጃ እና በማኅበር በማደራጀት የተሻለ ሥራ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
በመኖ አቅራቢዎች ችግር ምክንያት የመኖ እጥረት እያጋጠሙ መኾኑን አንስተው በሂደትም ጥብቅ ክትትል ተደርጎ የማስተካከል ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።
በከተማዋ የሚገኙ የቢራ ፋብሪካዎችን ከእንስሳት አልሚዎች ጋር በማሥተሳሰር ችግሩን ለማቃለል ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አንስተዋል።
የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ጥያቄ ያቀረቡ ባለሃብቶችን በፍጥነት ወደ ሥራ በማስገባትም የመኖ አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት እንደሚፈታ ጠቁመዋል።
የመሥሪያ ቦታ እጥረትንም ለመፍታት ከተማ አሥተዳደሩ በማኅበር በማደራጀት በክላስተር ደረጃ የመሥሪያ ቦታ እያመቻቸ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።
ለአብነትም ባለፈው ዓመት በዶሮ እና በወተት ላም እርባታ ለተሰማሩ ከ15 በላይ ኢንተርፕራይዞች ቦታ መሠጠቱን ጠቅሰዋል።
ነባር ባለሃብቶችም በቴክኖሎጅ አጠቃቀም፣ ምርትን በመጨመር እና በጥራት አጠባበቅ ዙሪያ ለአነስተኛ አንቀሳቃሾች ተሞክሮ እንዲያካፍሉ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የወተት ምርትን በጥራት እና እሴት በመጨመር ለገበያ ለማቅረብም በወተት ማቀነባበሪያ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የአንድ ቀን ጫጩት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት በከተማዋ ከሚገኘው የደብረ ሆላንድ ድርጅት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል። ለዚህም የማስፋፊያ ሥራ እየተሠራለት እንደሚገኝ ጠቁመው ሲጠናቀቅ ጫጩት በከተማዋ እንዲፈለፈል ለማድረግ ችግሩ እንደሚቀረፍ አመላክተዋል።
በምግብ ራሳችንን እንቻል ስንል የሌማት ቱርፋት መርሐ ግብርን በውጤታማነት መተግበር ነው ብለዋል። ለዚህም አልሚዎች ያለባቸውን ሌሎች ችግሮች እየተከታተልን ለመፍታት በቁርጠኝነት እንሠራለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበደብረ ብርሃን ከተማ የተሻሻሉ የበግ ዝርያዎችን በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው።
Next articleየእንቅስቃሴ ውስንነት በሚገድበው የሸማ ሥራ ለሌሎች ሰዎች ሥራ መፍጠር የቻለው ሥራ ፈጣሪ