
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሌማት ቱርፋት መርሐ ግብር የእንስሳት ዘርፉን ዘመናዊ በማድረግ እና ትርፋማነቱን በማሳደግ ላይ ትልቅ ትኩረት ያደረገ ነው።
የወተት ምርትን በመጨመር፣ የቆዳ እና የሥጋ ጥራትን በማሻሻል፣ የአርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ዓላማ ያደረገ ነው።
በተለይም በእንስሳት ሃብት ልማት ትኩረት ከተደረገባቸው ንዑስ ዘርፎች መካከል የወተት እና የሥጋ ምርትን በብዛት እና በጥራት ማሻሻል ተጠቃሽ ነው። ከእነዚህ ዘርፎች መካከልም የበግ ልማት አንዱ ተደርጎም ይወሰዳል።
በደብረ ብርሃን ከተማ በበግ እርባታ ከተሰማሩ ድርጅቶች መካከል ዜድ ኤም ጂ አንዱ ነው። የድርጅቱ ሥራ አሥኪያጅ ዩናታን ቢተው (ዶ.ር) የበግ እርባታ ውጤታማ ከኾኑት የእንስሳት ዘርፎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።
አካባቢው ለበግ እርባታ የተመቸ በመኾኑ ለሥጋ ውጤት እና ለእርባታ የተሻሉ የበግ ዝርያዎችን በማርባት ለገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙም ተናግረዋል። በየሦስት ወሩ ለገበያ እያቀረቡ እና እስከ ሞጆ ድረስ የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚ መኾናቸውንም ነው የተናገሩት።
እየተተገበረ ለሚገኘው የሌማት ቱርፋት መርሐ ግብርም በበግ ሥጋ ልማት ዘርፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ነው የገለጹት። ድርጅቱ ከበግ እርባታ በተጨማሪ በወተት እርባታ ላይም እየሠሩ መኾኑንም አብራርተዋል። ለ28 ቋሚ ሠራተኞች የሥራ እድል እንደፈጠሩም ነግረውናል።
ልክ እንደ ከብት እርባታ ሁሉ የበግ እርባታም የጤና ክትትል ከተደረገላቸው እና በቂ መኖ ከቀረበላቸው በአጭር ጊዜ ውጤታማ የሚያደርግ ዘርፍ ስለመኾኑም ጠቁመዋል። ወጣቶች ቢሰማሩ ተጠቃሚ መኾን እንደሚችሉ ነው የጠቆሙት።
በቀጣይም የዶሮ እርባታን በመጨመር በተሟላ የእንሥሣት ልማትን ለማስቀጠል እቅድ እንዳላቸው አመላክተዋል።
በደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል የእንስሳት እርባታ ከፍተኛ ተመራማሪ እና የበግ ምርምር አሥተባባሪ አየለ አበበ (ዶ.ር) ማዕከሉ በአካባቢው ያሉትን የበግ ዝርያዎች በምርምር እና በመደገፍ ለበግ እርባታው የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የተሻሉ ዝርያዎችን በመምረጥ እና በማዳቀል የበግ ምርታማነት እንዲጨምር እየተደረገ ነው ብለዋል። ለአብነትም የመንዝ፣ የዋሸራ እና የቦንጋ በጎችን በመረጣ እያሻሻሉ እና ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እያደረጉ መኾኑን ጠቅሰዋል።
በዘርፉ ለመሥራት በግልም ይሁን በማኅበር ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች በጥራት እና በቴክኖሎጅ አጠቃቀም ሥልጠናዎችን በመሥጠት ድጋፍ እያደረጉ ስለመኾኑም አንስተዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
