
ባሕር ዳር ፡ ታኅሣሥ 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) በወቅታዊዉ የጸጥታ ሁኔታ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።
ሙሉ መግለጫው ቀጥሎ ቀርቧል፦
በወቅታዊዉ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ከአዴኃን የተሰጠ መግለጫ
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሚታወቀው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) በቅርቡ ሶስተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ባደረገበት ወቅት ከድርጅታዊ መዋቅር ባለፈ በሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ጠለቅ ያለ ውይይት እና ምክክር ማድረጉን መግለጻችን ይታወሳል። በጉባዔው ከተነሱ አጀንዳዎች ውስጥ የክልሉ አሁናዊ አሳሳቢ የጸጥታ ሁኔታ እና የመፍትሔ አቅጣጫዎቹ ሰፊውን ጊዜ የወሰደ ነበር፤ በመጨረሻም ጉባዔተኛው ከነገሩ አሳሳቢነት እና ጥልቀት አንጻር በአጭር ጊዜ ውስጥ በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ድጋሚ ተወያይቶ መግለጫ ይሰጥ ዘንድ የቤት ሥራ ሰጥቶ ነበር:: በመሆኑም የ አዴኀን ሥራ አሰፈጻሚ ኮሚቴ በወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ እና መፍትሄዎች ዙሪያ የበሰለ ውይይት እና ምክክር አድርጓል። አዴኃን ሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው ህልቆ መሳፍርት መከራ ይቆም ዘንድ ቋሚ መፍትሄው ድርድር እና ውይይት እንደሆነ እያመላከተ በጊዚያዊነት እነዚህ ስድስት (6)ነጥቦች ላይ በሁሉም ኃይሎች በኩል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ያሳስባል።
1. በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የስርቆት ፣ የእገታ እንዲሁም የግድያ ወንጀሎች እጅጉን እየተበራከተ መጥቶ ማኅበረሰባችን በሰቀቀን ለመኖር ተገዷል፤ በመሆኑም የወንጀሉ ተዋናዮች እንዲለዩ ፣ ማኅበረሰባዊ ፍትሕ እንዲመጣ እና ሕዝባችንም አፎይታ እንዲያገኝ እንጠይቃለን።
2. እንደ ማዳበርያ፣ ምርጥ ዘር እና መሰል የግብርና ግብአቶች በግጭቱ ምክንያት በወቅቱ ማሰራጨት ባለመቻሉ የግብርና ምርት በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መጥቷል፤ የተመረተውም ቢሆን በመንገድ መዘጋት፣ በቀረጥ እና ዝርፊያ ምክንያት የገበያ ትስስሩ ስለተዳከመ ሕዝባችን እጅጉን ተጎድቷል። ስለሆነም ሁለቱም ኃይሎች በዚህ ዘርፍ ላይ ልዩ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እናሳስባለን።
3. ለማኅበረሰባችን ሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ ሚና ያላቸው በክልሉ በንግድ እና በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች የተሰማሩ ባለሀብቶች በተለዬ ሁኔታ ተጠቂ መሆናቸውን እና ይህን ሽሽትም ሥራቸውን ትተው ወደ ትልልቅ ከተሞች መፍለሳቸውን መረዳት ችለናል። ስለሆነም የሕዝባችንን ስቃይ ለመቀነስ ንግድ እና ኢንቨስትመንቶች እንዳይቋረጡ ለእነዚህ ባለሀብቶች ልዩ ጥበቃ እና ከለላ ይደረግ ዘንድ እናሳስባለን።
4. በብዙ የክልሉ አካባቢዎች በተለይ በገጠራማው ክፍል ላለፉት ሁለት ዓመታት ትምህርት ቆሞ እንደነበር በዚህም ትውልድ ተሻጋሪ ማህበራዊ ጉዳት እንደደረሰ ተረድተናል። በዚህ ዓመት በአንጻራዊነት የተሻለ ትምህርት የማስጀመር ሂደት እንዳለ የገምገምን ሲሆን ሂደቱ ምልዑ ይሆን ዘንድ እንጠይቃለን።
5. በጦርነቱ የሕዝብ ሃብት የሆኑ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት መስተናገዱን ለማወቅ ችለናል። በመሆኑም የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች ፣ ቤተ እምነቶች እና ቅርሶች ልዩ ጥበቃ እና ከለላ ይደረግላቸው ዘንድ እያስጠነቀቅን ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማትም በቶሎ እንዲጠገኑ እና ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ እናሳስባለን።
6. በመጨረሻም በክልሉ በሚደረገው ጦርነት ልዩ ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ያላቸው የውስጥና የውጭ ኀይሎች መኖራቸውን ታዝበናል። እነዚህ የሕዝባችን ጥንተ ጥላት የሆኑ ኃይሎች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ እያስጠነቀቅን ሕዝባችንም በአንክሮ እንዲከታተላቸው አደራ እንላለን።
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን)
ታኅሣሥ 06/2018 ዓ.ም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
