
ሁመራ፡ ታኅሣሥ 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ብቁ ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የትምህርቱን ዘርፍ በትኩረት እየደገፈ መኾኑን በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር አስታውቋል።
በዳንሻ ከተማ አሥተዳደር የዞኑ ከፍተኛ መሪዎች፣ የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች እና ነዋሪዎች በተገኙበት “እናት ዳንሻ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።
የመሠረት ድንጋዩን ያስቀመጡት የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው “የትምህርት መሠረቱ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ነው” ብለዋል። በመኾኑም እነዚህን ትምህርት ቤቶች ማስፋት ብቁ ትውልድ መገንባት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት ቤቱን ለመገንባት ሲነሳ ሕዝቡን እና ከውስጥ የሚያመነጨውን ሃብት በመተማመን ነው ያሉት አቶ አሸተ ገንብቶ ለመጨረስ የሁሉንም ወገን ትብብር ይፈልጋል ነው ያሉት።
ትምህርት ላይ በትኩረት መሥራት በዕውቀት፣ በክህሎት እና በአመለካከት ብቁ ትውልድ ለማፍራት ስለሚያስችል የትምህርቱን ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ እየደገፉ መኾናቸውን የከተማ አሥተዳደሩ ከንቲባ አብዱልዋሀብ ማሙ አስረድተዋል።
ከንቲባው አክለውም የሚገነባው ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት በ4 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ እንደሚያርፍ አንስተው ግንባታው ዘመኑን የሚመጥን ነው ብለዋል።
ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርትን ራሱን አስችሎ ማደራጀት እና ተማሪዎቹ የሚጠበቅባቸውን መስፈርት አሟልተው ከክፍል ክፍል መዘዋወር እንዲችሉ እንደሚያደርግ የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መምህር አምባቸው ንጉሱ ተናግረዋል።
ሕጻናት ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር ተቀላቅለው መማራቸው በርካታ ጫናዎች እንዲደርስባቸው ያደርጋል ያሉት ኀላፊው ራሱን በቻለ ትምህርት ቤት እንዲማሩ መሥራት ውጤቱ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቱ ሀገር ተረካቢ ሕጻናትን በእውቀት ማነጽ የሚያስችል በመኾኑ በግንባታው መጀመር ደስተኛ መኾናቸውን የሃይማኖት አባቶች እና ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቱን ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ ሀገር ወዳድ ወገኖች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ከተማ አሥተዳደሩ ጥሪ አቅርቧል።
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
