
ደባርቅ: ታኅሣሥ 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ታጥቀው በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት የሰላም አማራጭን ተቀብለው ገብተዋል።
ታጣቂዎቹ ሀገርን ከጉዳት እና ማኅበረሰብን ከጉስቁልና ለመታደግ የሰላም አማራጭን መከተል እንደሚገባም ነው የገለጹት።
የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ ላለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት መድረሱን አስታውሰዋል።
በዚህም በዞኑ በርካታ ማኅበራዊ አገልግሎቶች በሚፈለገው ደረጃ ተደራሽ ሳይኾኑ ቆይተዋል ብለዋል።
መንግሥት በሆደ ሰፊነት ልዩነትቶች በሠለጠነ እና ዘመኑን በሚመጥን ደረጃ በውይይት እንዲፈቱ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ነው ያሉት።
የሰላም አማራጭን የተከሉ ታጣቂዎችን በመቀበል መልሶ ለማቋቋም እና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየሠራን ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም እንደ ሀገር የደረሰውን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳት በመገንዘብ በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን በመከተል እየገቡ እንደኾነ ነው የገለጹት።
በቀጣይም እንደ መንግሥት የሰላም አማራጭን ለተከተሉ ኃይሎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ይሠራል ብለዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የሰላም አማራጭን የተከተሉ ታጣቂዎች በበኩላቸው የትጥቅ ትግል ዘመኑን የማይመጥን እና ሁለንተናዊ ቀውስን የሚያስከትል በመኾኑ የሰላም አማራጭን መከተላቸውን ተናግረዋል።
ታጣቂ ቡድኑ የሕዝብን ጥያቄዎች ከማስመለስ ይልቅ ግለሰባዊ ጥቅምን በማስቀደም እና ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በማበር እኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት እየሠራ ነው ብለዋል።
“ሰላምን መከተል መሸነፍ አይደለም፤ እንዳውም ለሀገር እና ለወገን ጥቅም ቅድሚያ መስጠትን የሚያሳይ ነው” ብለዋል።
ሌሎች በትጥቅ ትግል የሚገኙ አካላትም ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጡ እና ለሀገር እና ለወገን ያላቸውን ክብር እንዲያሳዩም ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
