በምዕራብ ጎንደር ዞን በጫካ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኀይሎች የሰላምን አማራጭ ተቀብለው ገቡ።

10

ገንዳ ውኃ: ታኅሣሥ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ከመጡ ታጣቂ ኀይሎች እና ከተሐድሶ ከተመለሱ ሠልጣኞች ጋር በገንዳ ውኃ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ እንደተናገሩት በዚህ ዓመት በዞኑ ሕግ የማስከበር ሥራ በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የሰላም አማራጭን በመዘርጋት ታጣቂዎች እንዲገቡ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

ተሐድሶ ለወሰዱ አካላትም የመቋቋሚያ ገንዘብ፣ የእርሻ ቦታ፣ በከብት ርባታ እና በሌሎች የሥራ ዘርፎች እንዲሰማሩ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

አዲስ የሰላምን አማራጭ ተቀብለው ለገቡ ታጣቂዎችም የመቋቋሚያ ገንዘብ እና ሌሎች የሥራ እድሎች እንደሚመቻችላቸው አስረድተዋል።

አሁንም የሰላምን አማራጭ ፈልጎ ለሚመጣ አካላት ምንግዜም በሩ ክፍት እንደኾነም ዋና አሥተዳዳሪው አሳስበዋል።

በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ እዝ ከፍተኛ አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ቾምቤ ወርቁ አሁን ላይ እንደ ክልልም ኾነ እንደዞን ሰላምን ለማፅናት በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።

ወደ ሰላም የመጡ አካላት ከሕዝቡ እና ከጸጥታ አካላቱ ጎን በመቆም የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ማስፈን ይገባቸዋል ብለዋል።

ሕዝቡ ለሰላም የሚደረገውን ርብርብ በማጠናከር ከዚህ ቀደሙ የተሻለ ሥራ መሥራት አለበት ብለዋል።

ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ለሰላም እጃቸውን እንዲዘረጉ ጀኔራሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ደረሠ አዱኛ በተሠራው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሥራ በርካታ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ ተቀብለው እየገቡ መኾኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ የሰላምን አማራጭ የተቀበሉትን ወደ ልማት ለማሰማራት በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ጠቁመዋል።

በዞኑ ከሥራና ክህሎት መምሪያ ጋር በመቀናጀት በርካታ የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል

ተመላሾችም መንግሥት በዘላቂነት ለማቋቋም ጥሩ ጅማሮ አሳይቶናል እና በቀጣይም በዘላቂነት ወደ ፊት ወደ ሥራና ልማት እንድንሰለፍ መንግሥት ሊደግፈን ይገባል ብለዋል።

የሰላምን አማራጭ ተቀብለው ከመጡ በኋላ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመኾን ሌሎች ወንድሞች እንዲገቡ አድርገናል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article‎ሰው ታሞ በገንዘብ ችግር ሳይታከም እንዳይቀር የጤና መድን ወሳኝ ነው።