‎ሰው ታሞ በገንዘብ ችግር ሳይታከም እንዳይቀር የጤና መድን ወሳኝ ነው።

8

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የማኅበራዊ ጤና መድኅን አገልግሎት የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

‎የመድረኩ ተሳታፊ መልአከ ኀይል ኤፍሬም ታደሰ የጤና መድኅን ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል።

‎የጤና መድኅን አገልግሎት ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ሁሉም አባል እንዲኾን ቢሠራ ጥሩ ነው ብለዋል።

‎የጤና መድኅን አገልግሎት መኖሩ የጤና ችግር ሲያጋጥም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

‎ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲኾን በመንግሥት በኩል አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ እና የመድኃኒት አቅርቦቱን መሻሻል እንዳለበት ተናግረዋል።

‎ሌላው ተሳታፊ የጣና ክፍለ ከተማ አሥተዳዳሪ ሙሉቀን ፈንቴ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት የዜጎች ጤናን በማሻሻል አገልግሎት የሚሰጥ የጤና ተግባር ነው ብለዋል።

‎ከፍለው መታከም የማይችሉ ሰዎች በዝቅተኛ ገንዘብ ታክመው የሚድኑ ነገር ግን ገንዘብ ባለመኖራቸው የሚሞቱ ዜጎችን ሕይወት የሚታደግ የጤና ኢንሹራንስ መኾኑን ነው የገለጹት።

‎የአገልግሎቱ ተደራሽ ያልኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ የከተማው መሪዎች እና ሚዲያ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሠራት አለበት ብለዋል።

‎የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ዓለም አሠፋ የጤና መድኅን አገልግሎት መረዳዳትን መሠረት ያደረገ፣ ሰው ገንዘብ የለኝም ብሎ ሳይጨነቅ በማንኛውም ጊዜ የጤና እክል ሲያጋጥም በጤና ተቋማት አገልግሎት የሚያገኝበት ሥርዓት ነው ስለመኾኑ ተናግረዋል።


‎የጤና መድኅን ከግለሰቦች 34 በመቶ ገንዘብ የሚሰብሰብ እና አብዛኛው ወጪ በመንግሥት የሚሸፈን እንደኾነ ተናግረዋል። ብዙ አባላት ኖረው የሚታከሙት ጥቂቶች ሊኾኑ ይችላሉ ያሉት ኀላፊዋ ሰው ታሞ በገንዘብ ችግር ሳይታከም እንዳይቀር የሚያደርግ መኾኑን ነው የገለጹት።

‎አባል የኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በዓመት አንድ ጊዜ በሚከፈል ገንዘብ ዓመቱን በሙሉ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ነው ያሉት።

‎ተጠቃሚዎች ውል ከተያዘበት የሕክምና ተቋም በሀገር ውስጥ ያሉ ሕክምናዎችን እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

‎በ2017 በጀት ዓመት 54 ሺህ አባላትን በማሳተፍ 173 ሺህ የማኅበረሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን እንዳገኙ ተናግረዋል። በተያዘው በጀት ዓመት 66 ሺህ አባላትን ለማሳተፍ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።

‎ለዚህም ማንኛውም የከተማው ነዋሪ አባል መኾን አለበት። አባል የኾነ ሰው ሁሉ ላይታከም ይችላል፤ ነገር ግን በሚዋጣው ገንዘብ ሌሎችን ሰዎች አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

‎ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleደብረ ብርሃን እንደ ሀገር ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገውን ሽግግር ማሳያ ማዕከል እየኾነች ነው።
Next articleበምዕራብ ጎንደር ዞን በጫካ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኀይሎች የሰላምን አማራጭ ተቀብለው ገቡ።