
የአስቸኳይ አዋጁ በክልሉ እኩል አለመተግበሩን የአማራ ክልል ኮሮናቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡ ግብረ ኃይሉ መመሪያ እና ደንቦች በትክክል እንዲተገበሩ አሳስቧል፤ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርቧል፡፡
በደብረ ታቦር፣ ወረታና ነፋስ መውጫ ከተማ አስተዳደሮችና ዓርብ ገበያ ከተማ እና በሌሎች የደቡብ ጎንደር ዞን አካባቢዎችም የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በትክክል እየተተገበረ አለመሆኑን አብመድ ታዝቧል፡፡ በኅብረተሰቡ ዘንድም ከፍተኛ መዘናጋት ይስተዋላል፤ አስፈጻሚ አካላትም ቢሆኑ የአዋጁን መመሪያ እና ደንቦች እያስከበሩ አይደለም፡፡
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ደረጃ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ እና የአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ሙሉነሽ አበበ (ዶክተር) በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጉራማይሌ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አዋጁ የወጣው በሁሉም አካባቢዎች እና የኅብረተሰብ ክፍሎች እኩል እንዲተገበር ቢሆንም በአስፈጻሚ አካላት ቁርጠኝነት እና በማኅበረሰቡ ንቃት ልዩነት ምክንያት አፈጻጸሙ ጉራማይሌ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ከፍተኛ መዘናጋት የሚታይባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል አስጠንቅቀዋል፡፡ ወረርሽኙ ሊያደርስ የሚችለውን የከፋ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ለማስቀረት ሁሉም አካል ያለምንም ቅድመ ሆኔታ ሕጉን በትክክል መተግበር እና ማስተግበር እንደሚገባውም መክረዋል፡፡ በተለይም አስፈጻሚ አካላት ማኅበረሰቡ የባሕሪ ለውጥ እስከሚያመጣ ሳይሰለቹ ማስተማር እና ሕግ ማስከበር እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ ኅብረተሰቡም የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልእክቶችን ተግባራዊ እንያደርግ እና ሕጉንም እንዲያከብር መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በሌላ በኩል የወረርሽኙ ስርጭት እየጨመረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚደረገው ድጋፍ እንዲጠናከርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ወረርሽኙ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለጉዳት መዳረጉን አስታውቀዋል፡፡ ስርጭቱ እየሠፋ መሄዱ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉንም አመላክተዋል፡፡ የተለያዩ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በመንግሥት ደረጃም ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ የተቋቋመው የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴም ድጋፎችን እያሰባሰበና እየሠራጨ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የተሰበሰበው ሀብት እና ፍላጎቱ የሚመጣጠን አለመሆኑን ነው ያነሱት፡፡
ወረርሽኙ መከሰቱ እንደረተረጋገጠ መጀመሪያ አካባቢ የሞቀ ድጋፍ የመረዳዳት ስሜት እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ሙሉነሽ አሁን ላይ መቀዛቀዙን አስታውቀዋል፡፡ ወረርሽኙ ስርጭት እየከፋ በሄደ ቁጥር ድጋፍ የሚያሻቸው ቁጥርም እየጨመረ ስለሚሄድ ተቋማት፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ የልሆኑ ድርጅቶች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
