የሕዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

6

አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ ውይይት በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር እየተካሄደ ነው።

እንደ ሀገር እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች የሕዝብን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ መኾናቸውን የተናገሩት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አሥፈጻሚ አባል ማስረሻ በላቸው ናቸው።

በሁሉም አካባቢዎች ያልተነካ እምቅ የመልማት አቅም መኖሩንም ገልጸዋል። የደብረ ብርሃን ወጣቶች ይህንን ፀጋ ጥቅም ላይ በማዋል በሀገራቸው ሠርተው ለመለወጥ በትጋት እና በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በሁሉም አካባቢዎች የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የሀገርን እድገት እና ብልጽግና ለማረጋገጥ መንግሥት እየሠራ እንደሚገኝ ያነሱት አቶ ማስረሻ በላቸው በአማራ ክልል ደብረ ብርሃን ከተማ የተከናወኑ እና በመከናወን ላይ ያሉ ሁሉን አቀፍ የልማት ተግባራት ለዚህ ጥሩ ማሳያ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ከግብርና በተጨማሪ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን እና በዲጂታል ልማት ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎች ለስኬት እንዲበቁ የጋራ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል።

የለውጡ መንግሥት አሳታፊና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የተረጋገጠባት ጠንካራ ሀገር የመገንባት ዓላማን ሰንቆ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። በዚህም እምርታዊ ውጤቶች ተመዝግቧል ነው ያሉት።

በመድረኩ የተሳተፉ የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአማራ ክልል ሕዝብ የፖለቲካ ተሳትፎ እና ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነቱ በተግባር እውን እየኾነ መኾኑን ተናግረዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የልማት ሥራ ወደ አምራችነት ለመሸጋገር የሚደረገው ጥረት እየተሳካ እንደኾነም አንስተዋል።

የሚነሱ እና አኹንም ያልተፈቱ ሌሎች የሕዝብ ችግሮችን በውይይት እና በጋራ ሥራ ተቀናጅቶ በመሥራት ለለውጥ መትጋት ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጤና መድኅን አገልግሎት የመረዳዳት እና የጤና ዋስትና የሚረጋገጥበት ትልቅ ተግባር ነው።
Next articleደብረ ብርሃን እንደ ሀገር ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገውን ሽግግር ማሳያ ማዕከል እየኾነች ነው።