
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የማኅበራዊ ጤና መድኅን አገልግሎት የንቅናቄ መድረክን እያካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በ2017 በጀት ዓመት በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት ከፍተኛ አፈጻጸም ካላቸው ዞኖች አንዱ መኾኑን ተናግረዋል።
እንደ ክልል የጤና መድኅን ዘላቂ የጤና ፋይናንስ ሥርዓትን ለመገንባት አንዱ መውጫ በር ነው ብለዋል። ለዚህም የአካባቢን ሃብት ማሰባሰብ እና የተሰበሰበውን በአግባቡ መጠቀም ቁልፍ ጉዳይ መኾኑን ነው የተናገሩት።
የረጅ ድርጅቶች ድጋፍ እየቀነሰ መጥቷል ያሉት ኀላፊው የጤና ሥርዓቱን ዘላቂ እና የማይበገር ለማድረግ ዘላቂ የኾነ የውስጥ የፋይናንስ አቅም መገንባት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ የጤና መድኅን ዋና መሣሪያ ነው ብለዋል።
ጤና መድኅን ፍትሃዊ የኾነ የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ለማዳረስ ቁልፍ ምክንያት ነው፤ “የመረዳዳት የጤና ዋስትና የሚረጋገጥበት ትልቅ ተግባር መኾኑንም” ነው የገለጹት።
በዚህ ዓመት ሁሉም የከተማ ነዋሪ አባል እንዲኾን የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል። የጤና መድኅን ተግባራትን በቁርጠኝነት በመሥራት በአንድ ወር ውስጥ እንዲጠናቀቅ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በከተማ አሥተዳደሩ አገልግሎቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ አዳጊ ለውጦች መታየታቸውን ተናግረዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቦ ከ100 ሺህ በላይ ተጠቃሚዎች የሕክምና አገልግሎት እንዳገኙ ገልጸዋል።
አገልግሎቱ መታከም ለሚገባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ባለመደረጉ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሥራት ይጠይቃል ነው ያሉት።
የጤና መድኅን ተግባር ሰው ተኮር የኾነው የመረዳዳት ባህሪ የሚገለጽበት ነው ብለዋል። ለጤናው ሴክተር ፋይናንስን ከረጅዎች ለመላቀቅ ጤና መድኅን ላይ በሰፊው መሥራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
በየደረጃው ያሉ መሪዎች በቁርጠኝነት በመሥራት ተግባሩን ውጤታማ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በዛሬው ዕለት የከተማ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ በፋሲሎ ክፍለ ከተማ የከነማ መድኃኒት ቤት አገልግሎት አስጀምሯል። የክልሉ ጤና ቢሮም ዘመናዊ አምቡላንስ መኪና ለከተማ አሥተዳደሩ አስረክቧል።
ለተደረገው ድጋፍ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይዎት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
