ዘምዘም ባንክ አክሲዮን ማኅበር ከታክስ በፊት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን አስታወቀ።

20

አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዘምዘም ባንክ አክሲዮን ማኅበር 5ኛ መደበኛ 4ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል።

ባንኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም ማስመዝገቡን የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አስታውቋል።

የዘምዘም ባንክ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ ናስር ዲኖ (ዶ.ር) ባንኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከታክስ በፊት ከ1 ነጥብ 23 ቢሊዮን ብር በላይ ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

ባንኩ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች እንዲያሟሉ የደነገገውን የ5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ማሟላት መቻሉንም ገልጸዋል።

ባንኩ ወጣቶችን እና ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ብድር መስጠቱንም ነው የገለጹት። ዲያስፖራውን በባንኩ እንዲገለገል ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል። ዘምዘም ባንክ 64 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማሰባሰብ መቻሉን የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር አስታውቀዋል።

ዲያስፖራውን በባንኩ እንዲጠቀም የሚሠሩ ተግባራት የበለጠ እንደሚጠናከሩም ገልጸዋል። እስከ ተጠናቀቀው በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ 11 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

ከ18 ሺህ በላይ ባለአሲዮኖች ያሉት ዘምዘም ባንክ በብሔራዊ ባንክ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ኾኖ መመዝገቡን የቦርድ ሰብሳቢው ናስር ዲኖ (ዶ.ር) አስታውቀዋል።

የባንኩ አጠቃላይ ሃብትም ከ16 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተገልጿል።

ዘምዘም ባንክ በመላ ሀገሪቱ ከ1 ሺህ 732 በላይ ሠራተኞች ሲኖሩት በሥራ ፈጠራ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተም ይገኛል።

ዘጋቢ:- ተመስገን ዳረጎት

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleውጤታማዎቹ ዶሮ አርቢዎች
Next articleየጤና መድኅን አገልግሎት የመረዳዳት እና የጤና ዋስትና የሚረጋገጥበት ትልቅ ተግባር ነው።