
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እንድሪስ ፈንታው በደሴ ከተማ አሥተዳደር አምስት አባላት ያሉት ማኅበር አቋቁመው በዶሮ እርባታ ተሰማርተው እየሠሩ ነው። በ2016 ዓ.ም እንደጀመሩም ነግረውናል።
“ወባስ ብራውን” የተባሉ ምርጥ የዶሮ ዝርያዎችን ከኮምቦልቻ የዶሮ ፋብሪካ በማምጣት እያሳደጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል። እነዚህ ዝርያዎች በዓመት እያንዳንዳቸው እስከ 360 እንቁላል እንደሚጥሉ እና ምርታማ መኾናቸውንም ነው ያብራሩት።

አቶ እንድሪስ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ባዘጋጀው የዶሮ እርባታ ሼድ ተጠቃሚ ኾነዋል። በእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት በኩልም ባገኙት ሙያዊ ድጋፍ ውጤታማ መኾን እንደቻሉም ገልጸዋል። ከራሳቸው አልፎ ቤተሰቦቻቸውን እያሥተዳደሩበት እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ሌላኛው በዶሮ እርባታ ዘርፍ ተሠማርቶ ያገኘነው ወጣት በጸሎት መለሰ በማኅበር በመደራጀት ሥራውን በ300 ዶሮዎች ጀምረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ2 ሺህ በላይ እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን እየተንከባከቡ እና እንቁላል ለማኅበረሰቡ በማቅረብ ተጠቃሚ መኾናቸውን ነው የገለጸው።
በቀጣይ ዘመናዊ የዶሮ እርባታ ዘዴን በመጠቀም በተሻለ መንገድ አሥፋፍቶ ለመሥራት በሂደት ላይ መኾናቸውንም ነው የተናገረው።
ዘርፉ በትንሽ ቦታ እና ገንዘብ በመጀመር ብዙ መሥራት የሚያስችል በመኾኑ ወጣቱ በዚህ ዘርፍ ቢሰማራ ውጤታማ መኾን እንደሚቻል አስተያየቱን ሰጥቷል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፈቃደ ጸጋው በከተማ አሥተዳደሩ የእንስሳት ሃብት ልማትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የዶሮ እርባታ እና የእንቁላል ምርትን በማሳደግ በኩልም የሌማት ቱርፋት መርሐ ግብርን ውጤታማ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን ጠቁመዋል።
በከተማዋ በአንድ ቀን ጫጩት ማሳደግ 40 ኢንተርፕራይዞች፣ በእንቁላል ጣይ ዶሮ ማርባት ስድስት ኢንተርፕራይዞች በሥራ ላይ መኖራቸውን ለአብነት አንስተዋል። ዘርፉ የቅርብ ክትትል የሚፈልግ በመኾኑ በቅርበት የባለሙያ ክትትል እና ድጋፋ እየተደረገ እንደሚገኝም ነው ያመላከቱት።
የበለጠ ውጤታማ እንዲኾንም የመሥሪያ ቦታ የሚኾኑ ሼዶችን ገንብቶ ለዶሮ አርቢዎች በማስተላለፍ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
