
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዙ የቴክኖሎጂ ምርቶችን በማበልጸግ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በዚህም ለኮሮናቫይረስ ቅድመ መለያ የሚረዳ አውቶማቲክ የተቀናጀ የሙቀት መለኪያ መሳሪያ ተግባራዊ ማድረጉን ነው ያስታወቀው፡፡ ይህም ከተለመዱት የሙቀት መለኪያዎች የተለየ እና የብዙ ሰዎችን የሙቀት መጠን ያለንክኪ በመለካተ፣ በማከማቸት እና በመተንተን ለሚመለከተው አካል መረጃዎችን የሚሰጥ መሆኑን ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡
የሙቀት መለኪያ መሳሪያው ከፍተኛ የውጭ ምዛሬን የሚያስቀር መሆኑንም አመላክቷል፡፡ ከዚህ ባለፈ ከውጭ ሀገራት የሚገቡ መሳሪያዎች መቀያየሪያቸው በስፋት ስለማይገኝ ቢበላሹ እንኳ ከአገልግሎት ውጪ እንደሚደረጉ የገለጸው ኤጀንሲው ይህን ችግር ለመቅረፍ እንደሚያግዝም ነው ያሳወቀው፡፡
በኤጀንሲው የተሰራው መሳሪያ አካል ጉዳተኞች ያልተመቸ የነበረውን ከዚህ ቀደም ተግባራዊ የተደረገውን መሳሪያ ችግር እንደሚቀርፍም ተገልጧል፡፡ ለሰዎች እና ለተሽከርካሪዎች አገልግሎት የሚሰጥ በኬሚካሎች አማካኝነት በራሱ የሚያጸዳ መሳሪያ ተግባራዊ ማድረጉንም የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡
ምርቶችን ከትራንስፖር እና ከጤና ሚኒስቴር ጋር ስምምነት በማድረግ ለኤርፖርት፣ ለድንበር አካባቢ እንዲሁም ሰው በሚበዛባቸው አካባቢዎች ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝም በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ አስታውቋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
