ጤናማ ትውልድን ለመገንባት የጤና ተቋማትን አገልግሎት መደገፍ እና ማሻሻል ይገባል።

7

ደባርቅ: ታኅሣሥ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ እና የሰሜን ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ በጋራ ለበየዳ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት የአንቡላንስ ድጋፍ አበርክተዋል።

በርክክብ መርሐ ግብሩ የተገኙት የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ ዞኑ ለጤናው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በወረዳ የጤና ማዕከላት የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት የተሳለጠ እና ማኅበረሰቡን ከጉዳት የሚታደግ እንዲኾን ለማስቻል የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

“ጤናማ ትውልድን ለመገንባት የጤና ተቋማትን አገልግሎት መደገፍ እና ማሻሻል ይገባል” ያሉት ዲያቆን ሸጋው ይሄንንም ተግባር ለማከናወን መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል።

ድጋፎችን ከማድረግ በዘለለም ለማኅበረሰባዊ አገልግሎት ተብለው የሚበረከቱ ቁሳቁሶችን ለታለመላቸው ዓላማ በአግባቡ እንዲውሉ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራ እንደሚሠራም አንስተዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ልዑል ብርሃን ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ አንድ አንቡላንስ ለበየዳ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል። ይሄም ድጋፍ የእናቶች እና ሕጻናትን ሞት በዘላቂነት ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት አንድ አካል እንደኾነ ነው የገለጹት።

ወረዳው ከዞኑ ማዕከል በአንጻራዊነት በርቀት የሚገኝ እና ለትራንስፖርት አገልግሎት አስቸጋሪ በመኾኑ ድጋፉ ችግሮችን ለማቅለል እንደሚያግዝ አብራርተዋል።

የበየዳ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሃብቴ አስማረ ድጋፉ በወረዳው ለሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል ብለዋል።

ከዚህ በፊት የአንቡላንስ ተሽከርካሪ እጥረት በመኖሩ የአካባቢው ማኅበረሰብ ይቸገር እንደነበር አስታውሰዋል። ድጋፉ ይሄን ችግር ለማቃለል መፍትሔ ነውም ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደላላ ነገር…
Next articleሕዝባዊ ውይይት በደብረ ብርሃን ከተማ እየተካሄደ ነው።