የደላላ ነገር…

5

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት እና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ባዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደላላን “ገንዘብ እየተከፈለው ፈላጊ እና ተፈላጊን ፣ ሻጭ እና ገዥን፣ አከራይ እና ተከራይን አገናኝ፣ አስማሚ ” በማለት ተርጉሞታል።

በ2013 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣው የኢትዮጵያ ንግድ ሕግ አንቀጽ 54 ደግሞ ደላላ ሥራ እና ሠራተኛን፣ ሻጭ እና ገዥን ወዘተ በማገናኘት በድለላ የተመጣጠነ ክፍያ የሚያስገኝ ሙያ ነው ሲል ተንትኖታል።

ደላላ በአምራቹ እና በጅምላ አቅራቢው ወይም በችርቻሮ ነጋዴው፣ በአጓጓዡ፣ በገዢው እና በሻጩ መካከልም የማይጠፋ ሰው ኾኖ እናገኘዋለን።

ዕውን ደላላ በተመጣጣኝ ሒሳብ ፈላጊን እና ተፈላጊን እያገናኘ ነው? ከገንዘብ ይልቅ ሰብዓዊነትን እና የኢትዮጵያዊነት እሴትን ተላብሶ እየተገበረ ነው? የትዝብታችን ማጠንጠኛ ጭብጥ ነው።

ከላይ ለቀረበው ጥያቄ ምላሹን ከሞላ ጎደል እነኾ!

የጓዳኛዬ ቤተሰቦች የቤት ሠራተኛ መቅጠር ይፈልጋሉ። ተፈላጊዋን ሠራተኛ ለማግኘትም የግድ ደላላ ጋር መሄድ ነበረባቸው። እናም በጠቋሚ ወደ አንድ ሁነኛ ደላላ ይሄዱና በቅድመ ሁኔታው ተነጋግረው ተግባቡ።

ደላላውም የሚያስከፍለውን ዋጋ በመንገር በውስን ቀን ውስጥ የቤት ሠራተኛ እንደ ሚያመጣላቸው ይነግራቸዋል።

በሀሳብ ተስማሙ። ደላላውም ቃሉን አላጠፈም።

በድለላ የመጣችው ሠራተኛ ለተወሰኑ ወራት እንደ ንብ ባተሌ ኾና እንደ እንዝርት እየሾረች የውዴታ ግዴታዋን አከናወነች። ቀስ በቀስ ግን ያ ትጋቷ ወረደ። እያሰለሰች “ታመምሁ” በሚል ከምትሠራበት እየቆዘመች የምትቀመጥበት ቀን በዛ።

አሠሪዎቿም በሰብዓዊነት ተጨነቁ። ሐኪም ቤት እንሂድ ሲሉም ጠየቋት። ልጅቷ ግን የሆዷን በሆዷ ይዛ መታከምን አሻፈረኝ አለች። ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? ሲሉ አማከሯት። ህመሙ አዲስ አለመኾኑን ጠቁማ መፍትሔው ሀገር ቤት በመሄድ ባሕላዊ መድኃኒት መውሰድ እንደኾነ ተናገረች።

አሠሪዎቿም አላመኗትም፤ ለደላላው በመደወል ሁኔታውን ይነግሩታል። እርሱም ሆድ ሲያውቅን ብሒል አርግዞ ገጠር ሄዳ ባሕላዊ መድኃኒት እንድትወስድ እንዲፈቅዱላት ጠቆማቸው።

አሠሪዎቿም “ይሁን!”ብለው ሁኔታዎችን ሁሉ አመቻቹላት። ከደመወዟ ላይ ተጨማሪ ለሕክምና የሚኾናትን ገንዘብ ደጉመው ላኳት።

ከተወሰኑ ቀናት በኋላ አሠሪዋ እና ገጠር ሄድሁ ያለችው ልጅ ከተማ ውስጥ ዓይን ለዓይን ተገጣጠሙ። ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላም ከህመሟ አገግማ መኾኗን ጠየቋት። ምን ብትል ጥሩ ነው?

አልታመምሁም እኮ። ደላላው በተሻለ ደመወዝ ሌላ ቤት ላስገባሽ ብሎ ነው ሰበብ ፈጥሮ የወሰደኝ ብላ ተናገረች።

“ድንቄም ደላላi” አትሉም። የደላላው ነገረ ሥራ የመተማመን እሴታችን ምን ያህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደተሸረሸረ እና ውኃ እንደበላው ጠቋሚ ነው እላለሁ።

ሌላ አንድ ሽንኩርት እና አትክልት ቸርቻሪ ሳያስቡት ስለ ደላላ ያወጡትን የተደበቀ እውነት በአስረጅነት ልጨምር።

ቸርቻሪውን ገበያተኛው ከወገቡ ዝቅ ብሎ ሽንኩርት እያነሳ አንድ ኪሎ ግራም ቀይ ሽንኩርት ዋጋው ስንት ነው? ብሎ ይጠይቃቸዋል። 45 ብር ሲሉ ይመልሳሉ።

ገበያተኛውም ኧረ ዋጋው በዛ! 30ም አይደል!? ይቀንሱ” በማለት ይከራከራቸዋል።

“አምስቱ ብር እኮ የደላላው ነው” ቸርቻሪው ይመልሳሉ።

ደላላው ከኩንታል በአምስት ብር ሂሳብ አስቦ ወስዷል”ብለው ተናገሩ። አያችሁ አይደል ገበያ በደላላ እንዴት እየተዘወረ እንደኾነ!

አርሶ አደሩ ያመርታል። ያውም በዓመት ከሁለት ጊዜ እና በላይ። ገበያውም አልተራበም። የግብርና ምርቶች እና የፋብሪካ ውጤቶች ዋጋ ግን በየዕለቱ እያሻቀበ ነው።

“ለምን?”

ኅብረተሰቡ ደግሞ በኑሮ ውድነቱ ከመንገብገቡ ባለፈ ጣቱን መንግሥት ላይ እየቀሰረ ነው። ግን አቅርቦት እያለ ለዋጋ መናር ምክንያቱ የገበያ ዋጋ በደላላ መተመኑ እምብዛም የተረዳው አይመስለኝም።

ሀቁ ግን ገበያው እየተመራ ያለው በአምራች እና አቅራቢው ብቻ ሳይኾን የደላላውም እጅ አለበት ባይ ነኝ።

ደላላ ገበያው እሳት እንዲኾን፣ ምርት እንዲከዘን ወይም ዋጋ እንዲጨምር ዓይነተኛ ምክንያት ነው ለማለት ያስደፍራል።

በአፍቅሮተ ንዋይ የተስገበገቡ እና በአቋራጭ መክበርን ዓላማ ያደረጉ ደላላዎች የገበያ ዋጋን እንደፈለጉ እየቆረጡ ዜጋው በከፍተኛ ሁኔታ በኑሮ ውድነት እንዲሰቃይ ማድረጋቸውን እዚህም እዚያም ይነሳል።

ሌላ አንድ ማሳያ ላቅርብ፤ ደላላው በአንደበቱ የነገረኝ ነው። አንድ ግለሰብ ቤት መግዛት ይፈልጋል፤ እናም ከደላላው ጋር ተገናኘ፤ የሚፈልገውን የቤት ዓይነት እና የቦታ ሥፋት ለደላላው ይነግረዋል።

ደላላውም የተባለውን ዓይነት ቤት እና የቦታ ስፋት በእግር በፈረስ አፈላልጎ አገኘ። አስቀድሞም ሻጭን የድለላ ሒሳብ እንደማይጠይቃቸው ያሳምናቸዋል።

በምትኩም ሻጭ ካቀረቡት ዋጋ ላይ የራሱን ሂሳብ አክሎ ቤቱን እንደሚሸጥላቸው ያግባባቸዋል።

ቤቱንም ለገዥ አሳይቶ ይወዱታል። የሰውየውን መሻት የተረዳው ደላላ ገዥ በቀረበው ዋጋ ቤቱን ፈጥነው የማይገዙት ከኾነ ሌላ ገዥ በዚሁ ዋጋ ለመግዛት የቀረበ መኾኑን በእብለት ይነግራቸዋል።

ገዥም ቤቱን ፈልገውት ነበር እና ሌላ ሰው ሳይቀድማቸው ከተባለው ዋጋ ላይ መጠነኛ ዋጋ በማስቀነስ ይገዙታል።

ደላላውም ከገዥ ላይ ለዓመት አስቤዛ መሸፈኛ የሚኾን ጥሩ ገንዘብ መሥራቱን አወጋን።

ይባሱንም በሚያሳዝን ሁኔታ የድለላ በሚል ከገዥው ሰው ገንዘብ መቀበሉን በጀግንነት ተረከልን።

ይህ እውነት በጣት የሚቆጠሩ ጥሩ ደላላዎች መኖራቸውን ባያስክድም ጥቂት የማይባሉ አዝን ባይ ቅቤ አንጓቾች መኖራቸውን ፍንትው አድርጎ ይጠቁመናል።

አንዳንድ ደላላዎች መዋሸትን፣ ማታለልን እና በአቋራጭ መክበርን ሙያ እስከ ማድረግ መድረሳቸውንም ይነግረናል።

ድለላ መዋሸት፣ መስረቅ፣ መዝረፍ፣ ማጭበርበር፣ መካድ፣ ጥሎ ማለፍ እየኾነ ነው እንድንል ከላይ የሰማናቸው ሀገር ያወቃቸው፤ ፀሐይ የሞቃቸው ታሪኮች ነጋሪዎች ናቸው።

አሁን ላይ ቁጥራቸው ትንሽ የማይባሉ ደላላዎች ሩጫቸው ሁሉ በላባቸው፣ በጉልበታቸው እና በዕውቀታቸው ሠርተው ለማግኘት ሳይኾን በማይጨበጥ እና በቀቢጸ ተስፋ ወገኖቻቸውን በማታለል በአቋራጭ መበልጸግ እየኾነ ነው።

ምስጉን ደላላዎች ሠርተው ራሳቸውን ብሎም ሀገራቸውን ለመለወጥ ሲታትሩ ሕገ ወጥ ደላላዎች ግን በየዘርፉ ዘው እያሉ በቅቤ ጠባሽ ምላሳቸው ጤፍ እየቆሉ ሀገርንም ወገንንም እያመሱ ይገኛሉ ባይ ነኝ።

እናስ? ካላችሁ እናማ እነዚህን በአቋራጭ መመንደግ የሚሹ ደላላዎች ዛሬ ላይ ሀይ ብሎ የሚገስጻቸው ከጠፋ ነገ ላይ ሸቀጣ ሸቀጥ እና የግብርና ምርትን ከመቀሸብ ባሻገር ከባንዳዎች ብሎም ከሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ኾነው ሀገር ማፈራረስ መሸጣቸው ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲተረማመስ ማድረጋቸው አይቀርም።

በመኾኑም ቀናኢ የኾነ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሕገ ወጥ ደላላዎችን ሴራ እና ደባ ለማምከን ጊዜው አሁን ነው ባይ ነኝ። ሳይቃጠል በቅጠል ነውና ነገሩ።

በሙሉጌታ ሙጨ

ሰላም!

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ማኅበረሰቡ የሰላም ዘብነቱን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
Next articleጤናማ ትውልድን ለመገንባት የጤና ተቋማትን አገልግሎት መደገፍ እና ማሻሻል ይገባል።