
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር “የጉባ ብስራቶች፣ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በሚል መልዕክት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱም ተሳታፊዎች ጥያቄ እና አስተያየቶች አንስተዋል። በተሳታፊዎች ከተነሱ ጥያቄዎች የሥራ እድል ፈጠራ ጉዳይ አንዱ ነው። ወጣቶች ራሳቸውን ለውጠው ሀገርን እንዲለውጡ መንግሥት ሥራ ከመፍጠር ባለፈ የተደራጀ ድጋፍ እና ክትትል እንዲያደርግ በተሳታፊዎች ተነስቷል።
ከዚህም ባለፈ ከደመወዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ በሸቀጦች ላይ እየታዬ ባለው ጭማሪ መንግሥት እርምጃ መውሰዱ የሚበረታታ ቢኾንም አሁንም አንዳንድ የኢንዱስትሪ ምርቶች እጥረት እየታየ መኾኑን አንስተዋል። የተጀመረውን ሕጋዊ ርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠይቋል።
ክልሉ ያጋጠመውን የሰላም ችግር ለመፍታት በቅንነት የሚሠሩ የመንግሥት አካላት እንዳሉ ሁሉ የተሰጣቸውን ኀላፊነት እንደ መልካም አጋጠሚ ተጠቅመው ችግር የሚፈጥሩትንም ለይቶ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብለዋል።
የሰላም እጦቱ ማኅበረሰቡን ለከፋ ችግር እያጋለጠው በመኾኑ መንግሥት የጀመረው ሰላምን የማረጋገጥ ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። የሃይማኖት አባቶች ሃይማኖታዊ ግብረገብነትን ለምዕመኑ ሊያስተምሩ እንደሚገባም ተነስቷል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እንዳሉት የክልሉ መንግሥት ብሎም ከተማ አሥተዳደሩ የጀመረውን ልማት እና ሰላም የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።
የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት በከተማ አሥተዳደሩ ምርት በሚደብቁ ነጋዴዎች ላይ የተጀመረው ርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል ግብረ ኀይል ተቋቁሞ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ ማኅበረሰቡ ሊተባበር ይገባል ብለዋል።
የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለመንግሥት ሠራተኞች ለማቅረብ ከተማ አሥተዳደሩ እየሠራ ይገኛል ብለዋል። ምርቶችን በቀላሉ ማግኘት የሚያችል ዘመናዊ መጋዝን መገንባቱንም ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ የሥራ እድል ለመፍጠር ከታቀደው ከ48 ሺህ በላይ ወጣቶች እስከ አሁን ከ15 ሺህ በላይ ለሚኾኑት የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን አንስተዋል።
በቀጣይ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዩች ዋነኛው ተግባር ኾኖ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። እውነተኛ ሥራ ፈላጊዎችን ለይቶ የሥራ እድል የመፍጠር ችግር መኖሩንም ገልጸዋል። ከዚህም ባለፈ በሱስ የተጠቁ ወጣቶችን ከገቡበት ችግር እንዲወጡ እየተሠራ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
