የአማራ ሕዝብ ከዚህ በላይ በመከራ እና በስቃይ ውስጥ መኖር ይበቃዋል።

4

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከፍኖተ ሰላም፣ ከጅጋ ከተማ እና ከጃቢ ጠህናን ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በፍኖተ ሰላም ከተማ ተወያይተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሕዝብን ለከፋ ችግር መዳረጉን ተናግረዋል። ሕዝብ በነጻነት ሠርቶ እንዳይለወጥ፣ በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ ማድረጉን ገልጸዋል።
ከዚህ በላይ ይበቃል፤ ጽንፈኝነትን አንተጋስም፣ ጽንፈኛንም አንሸከምም ብለዋል።

ታጣቂውን ቡድን የሚደግፍ እና መረጃ የሚያቀበል የመንግሥት አካል እንዳለም አንስተዋል። ታጣቂ ቡድኑን እንዲቆይ ያደደረገው እና የክልሉን ግጭት ያራዘመው በመንግሥት አካል ውስጥ ኾኖ የሚደግፈው፣ መረጃ የሚያቀብለው በመኖሩ ነው፤ የመረጃ ምንጩ ከደረቀ እና ከውስጥ ኾኖ የሚደግፈው ከሌለ የመቆየት አቅም የለውም ነበር ነው ያሉት።

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የውስጥ አርበኞችን ማጽዳት እንደሚገባም አመላክተዋል። የአማራ ሕዝብ ከዚህ በላይ በመከራ እና በስቃይ ውስጥ መኖር ይበቃዋል ብለዋል።

ታጣቂው ኀይል ትውልድን ከትምህርት ገበታ ያራቀ፣ ልጆቻችን ወደ ኋላ እንዲመለሱ እና ተስፋ እንዳይኖራቸው ያደረገ ነው ብለዋል።

ሁሉም ሰላም ላይ መሥራት አለበት፤ በጫካ ያሉትን እየመከርን እናምጣቸው ነው ያሉት። የሰላም አማራጭን የሚቀበሉትን በተገቢው ማሠልጠን እና ማቋቋም እንደሚገባም ተናግረዋል።

የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለሕዝብ ሲሉ የእውነት መምከር እና ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት በየቀበሌው እየተመላለሰ ሰላምን ለማረጋገጥ እያደረገ ላለው ተጋድሎ አድናቆትም ክብርም አለን ነው ያሉት። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሀገር ሰላም እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የሚፈታው በአፈሙዝ ሳይኾን በውይይት እና በምክክር መኾኑንም ገልጸዋል። የምዕራብ ጎጃም ዞን ሕዝብ ሰላም የጠማው ነው ብለዋል። የጸጥታ ችግሩ ባለሃብቶችን ከአካባቢው እንዲርቁ ማድረጉንም ገልጸዋል።

ለሰላም ካልሠራን ሁሉም ነገር አይሳካም፤ የልማት ጥያቄ የሚፈታው ሰላም ሲረጋገጥ ነው፤ ሰላምን ለማረጋገጥ በጋራ እንሥራ፣ አንድነታችንን እናጠንክር ነው ያሉት። ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚገባም ተናግረዋል። መገዳደል ይበቃል፤ ሁሉም ልጆችን ይቆጣ ነው ያሉት።

የውስጥ አንድነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን ከፍታ ማረጋገጥ፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር እና የቀደመ የባሕር በሯን እንድታገኝ ማድረግ ይገባናል ብለዋል። ውስጥ ላይ ያለው ግጭት ሀገርን የሚያሳንስ እና ለውጭ ጠላት አሳልፎ የሚሠጥ መኾኑን ገልጸዋል።

አሁን ታጣቂ ቡድኑ ደክሟል፤ በጋራ እንነሳ እና በሰላም የሚገባ ከኾነ በሰላም እንዲገባ እናድርገው፣ በሰላም አልገባም የሚለውን ግን ታግለን አደብ እናስገዛው ነው ያሉት።

ሕዝብን ያማረሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች መፍታት እንደሚገባም ተናግረዋል።ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚገባም ገልጸዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል መላኩ ገላነህ መሪዎች ራሳቸውን ከጽንፈኝነት እና ከወላዋይነት በመውጣት ለሰላም መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል። ከታጣቂ ቡድኑ ጋር የሚሠራ መሪ መታረም አለበት ነው ያሉት።

ሰላም እንዲረጋገጥ ከጽንፈኝነት አስተሳሰብ መውጣት እና በጋራ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ሰላም እንዳይረጋገጥ በሚሠሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስዱም አስገንዝበዋል።

ለታጣቂ ቡድኑ መረጃ የሚያቀብል ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል። በለም መሬት ላይ ተቀምጦ ሳለ በሰላም እንዳያለማ የተደረገው ሕዝብ በችግር ውስጥ እንዲቆይ አንፈቅድም ነው ያሉት።

የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ ሕዝብ አስተካክሉ የሚለንን እናስተካክላለን ብለዋል። ሰላምን ለማረጋገጥ ከሕዝብ ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም ተናግረዋል። ለእውነተኛ ሃሳባችሁ፣ ለእውነተኛ ሰላም ፈላጊነታችሁ እና ለሰላም መስፈን ላሳያችሁት መነሳሳት እናመሰግናለን ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶች ሰላምን ለማረጋገጥ እያደረጉት ያለውን ጥረት እናደንቃለን ያሉት አሥተዳዳሪው በሃይማኖት ስም የሚነግዱትን እና ከታጣቂ ቡድኑ ጋር የሚሠሩትን ደግሞ ማረም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ብልሹ አሠራርን እና ሕገወጥነትን ለመከላከል በቁርጠኝነት እንደሚሠራም አንስተዋል። በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለው ወደ ሰላም ይምጡ፣ ለጋራ ሰላም በጋራ እንሥራ ብለዋል።

ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ፍላጎታችን ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የዜጎችን ሕይወት ማሻሻል ነው” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)
Next articleዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ማኅበረሰቡ የሰላም ዘብነቱን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።