“ፍላጎታችን ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የዜጎችን ሕይወት ማሻሻል ነው” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)

5

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ምየክልል እና የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከፍኖተ ሰላም፣ ከጅጋ ከተማ እና ከጃቢ ጠህናን ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በፍኖተ ሰላም ከተማ ተወያይተዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሩ ሌትናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ እውነት ጊዜዋን ጠብቃ እየወጣች ነው ብለዋል። ከአሁን በፊት የነበሩ ማደናገሪያ ሃሳቦች እየጠሩ ሕዝቡም እውነቱን እየተረዳ መምጣቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ብዙ ጠላቶች ያሏት እና የሚፈትኗት መኾኗንም ተናግረዋል።

ጠላቶች ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንድትኖር አይፈልጉም፣ ይህ ካልኾነ ደግሞ ጥቅማቸውን የሚያስከብርላቸው ተላላኪ የኾነ መንግሥት እንዲኖራት ይፈልጋሉ ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ሰላምን ከኾነች እድገት ይመጣል፤ እድገት ከመጣ ደግሞ ከእኛ በላይ ይኾናሉ ብለው ይሰጋሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች በተደጋጋሚ ያደረጉት ጦርነት በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ክንድ ተመትተው መመለሳቸውንም አስታውሰዋል።

በቀጥታ ጦርነት ያልተሳካለቸው ሀገራት ኢትዮጵያን ማፍረስ የሚቻለው የውስጥ ባንዳዎችን በማስነሳት ነው የሚል ስትራቴጂ ቀይሰው እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ባንዳ በየዘመናቱ እንደነበረ የተናገሩት አዛዡ አሁንም ለጠላት የሚላላክ ባንዳ መኖሩን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ሀገርን አሳልፈው ለጠላት የሚሰጥ ድርጊት እየፈጸሙ ነው ብለዋል። ለሕዝብ የሚጠቅም ዓላማ እና ግብ እንደሌላቸውም ተናግረዋል። የክፋት ተልዕኮ እየከሸፈ፣ እውነት እየተገለጠ መኾኑን ገልጸዋል። የክልሉ የሰላም ሁኔታ መሻሻሉንም ተናግረዋል።

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሕዝቡ በየጎሬው የተደበቀውን ታጣቂ እንዲያጋልጥም አሳስበዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ደግሞ እየተከታተለ ሕግ ያስከብራል ነው ያሉት። ነዋሪዎች የአካባቢያቸውን ሰላም ተደራጅተው እንዲጠብቁም አስገንዝበዋል።

የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ግፊት እንዲያደርጉም አሳስበዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል እየወሰደው ያለውን ኦፕሬሽን እንዲደግፉም አስገንዝበዋል። ትምህርት ቤቶች በፍጥነት ወደ መማር ማስተማር መግባት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

ሰላም እንዳይረጋገጥ በሚያደርጉ አካላት ላይ መረጃ እና ማስረጃ ላይ የተመሠረተ እርምጃ እንደሚወሰድም ገልጸዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) ለሰላም ያሳያችሁት ተነሳሽነት የሚያስመሰግን እና ክብር የሚሰጠው ነው ብለዋል። የምዕራብ ጎጃም አካባቢ ለም መሬት ያለው ለሌሎች አርዓያ የሚኾን ነበር ያሉት አሥተባባሪው ባለፉት ዓመታት ግን ለከፋ ችግር ተዳርጎ ቆይቷል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያን መመገብ የሚችለው ዞን ተጎሳቅሎ፣ ማኀበራዊ ግንኙነቱ ተቋርጦ ቆይቷል ነው ያሉት።

እኛ ፍላጎታችን ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የልማት ሥራዎቻችን በማፋጠን የዜጎችን ሕይወት ማሻሻል ነው፤ ሕዝቡ በነጻነት እንዲያለማ ነው፤ የታጣቂዎች ፍላጎት ግን ሕዝብ እንዳይንቀሳቀስ፣ ልጆች እንዳይማሩ ማድረግ እና ዘረፋ ነው ብለዋል።

ሰላምን ለማረጋገጥ ታጣቂዎች ለሰላም እንዲመጡ ማድረግ እና አካባቢያቸውን እንዲጠብቁም አሳስበዋል። በዘረፋ የተሳማረውን የጥፋት ኃይል መታገል እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

የሃይማኖት አባቶች ሃይማኖቱ የሚፈቅደውን እና ለእውነት መሥራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

ሕዝቡ በመተባበር፣በመደጋገፍ እና ሰላምን በማረጋገጥ ምዕራብ ጎጃም ወደሚታወቅበት ልማት እንዲመጣ ማድረግ እንደሚገባቸውም አንስተዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየውጭ ኀይሎች ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ እንዳትጠቀም ያቀዱት ሴራ ከሽፏል።
Next articleየአማራ ሕዝብ ከዚህ በላይ በመከራ እና በስቃይ ውስጥ መኖር ይበቃዋል።