
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር “የጉባ ብስራቶች፤ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በሚል መሪ መልዕክት ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ.ር)፣ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እና ሌሎች ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
በውይይቱ የተገኙት የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ እንዳሉት ኢትዮጵያ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ከማጠናቀቅ ባለፈ በቢሊዮን የሚገመቱ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን እያከናወነች ትገኛለች።
በተለይም ደግሞ ባለፉት ሦስት ዓመታት ለስንዴ ልማት በተሰጠው ትኩረት በየዓመቱ ታወጣ የነበረውን እስከ 1 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ማስቀረት ተችሏል ብለዋል። ከተሞችን ጹዱ እና ምቹ በማድረግ ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲኾኑ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል።
ሚኒስትሩ እንዳሉት ኢትዮጵያ ወንዞቿን እና ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶቿን እንዳትጠቀም፤ ወደ ቀይ ባሕር እንዳትጠጋ የውጭ ጠላቶች ከጥንት ጀምሮ ሀገሪቱን ሲያተራምሱ ቆይተዋል፤ አሁንም እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል።
ይህ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሀገር የማፍረስ ሴራ በራሳቸው በኢትዮጵያውያን አንድነት መክሸፉንም ገልጸዋል።
ለሀገሪቱ ሰላም ጠንቅ የኾኑ ጉዳዮችንም በመለየት ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። በአብሮነት እና አንድነት ላይ የተሠሩ የተዛቡ ትርክቶችን የማስተካከል ሥራ መሠራቱንም በማሳያነት አንስተዋል። የሚነሱ ችግሮችን በሰላማዊ እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት እንዲቻል ውይይትን ባሕል ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) የአማራ ሕዝብ ከሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በመኾን ሀገርን እንዳጸናው ሁሉ አሁንም ከሌሎቹ ወንድሞቹ ጋር በመኾን ለሀገረ መንግሥት መጽናት የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
በሀገሪቱ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት ሀገራዊ የምክክር መድረክ አዘጋጅቶ የምክክር ሥራ እየተሠራ ይገኛል። የአማራ ሕዝብም አሉኝ የሚላቸው ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱለት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
