
ደሴ፡ ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በገቢዎች ሚኒስቴር የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በ2017 በጀት ዓመት ግብራቸውን በታማኝነት ለከፈሉ ግብር ከፋዮች እውቅና ሰጥቷል፡፡
የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ 12 ግብር ከፋዮች በፌድራል ደረጃ የፕላቲንየም፣ የወርቅ እና የብር ተሸላሚ ሲኾኑ 28 ግብር ከፋዮች ደግሞ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡
እውቅና እና ሽልማት የተሰጣቸው ግብር ከፋዮች ግብር መክፈል ሀገራዊ ግዴታ መኾኑን ገልጸው፣ የተሰጣቸው እውቅናም ለቀጣይ ሥራ መነቃቃትን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ግብር ከፋዮችም የግብር ግዴታቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) በሀገሪቱ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠልና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ግብርን በአግባቡና በወቅቱ መክፈል እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
እውቅና የተሰጣቸው ግብር ከፋዮችም ለግብር ሕግ ተገዥነታቸውን በማረጋገጥ ለሌሎችም አርዓያ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ግብራቸውን በአግባቡ የማይከፍሉ ግብር ከፋዮችም ግዴታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ አወል አብዱ እውቅና የተሰጣችው ግብር ከፋዮች የዘመናችን የልማት አርበኞች ናቸው ብለዋል፡፡
በቀጣይም ግብር የመክፈል ባሕልን በማጠናከር ሀገር ወዳድ ዜጎችን ማፍራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር ድኤታ ዳዊት ውብሸት በ2018 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሠብሠብ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በወቅቱ እና በአግባቡ እንዲከፍሉም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ግብር ከፋዮችን ለማበረታታትም እውቅና እና ሽልማት እየተሰጠ መኾኑን ተናግረዋል።
ግብርን በአግባቡ ለመሠብሠብም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣን አሠራር በመተግበር ላይ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ:- ሰይድ አብዱ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
