
ጎንደር: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ” የጉባ ብስራቶች፣ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ ውይይት ተካሄዷል።
በውይይቱ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ ሌሎች የክልል እና የከተማዋ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ምክክሩ በዋናነት እየተሠሩ ያሉ የልማት ተግባራትን ለማስቀጠል እና ሕዝብ የሚያነሳቸውን የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ያለመ ነው።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ለልማት “ተባባሪ የኾነው የጎንደር ሕዝብ በልማት ሥራዎች የበኩሉን እየተወጣ መኾኑን” ተናግረዋል።
ጎንደርን ወደፊት ለማስቀጠል እና የበለጠ ለማልማት ዘላቂ ሰላም አስፈላጊ መኾኑን ያነሱት አቶ ቻላቸው ሰላምን ለማረጋገጥ በጋራ መሥራት የሚያስፈልግ መኾኑን ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ.ር) በጎንደር ከተማ እየተሠሩ ያሉ የልማት ተግባራት የከተማዋን ታሪካዊነት የሚያሳዮ መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
ሰላምን ለማረጋገጥ መንግሥት የሚሠራው ሥራ ብቻ በቂ አይደለም ያሉት ዶክተር ዲላሞ መሪዎች እና ሕዝቡ ከፍተኛ ትስስር ፈጥረው ሊሠሩ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) በጫካ የወጡ ወንድሞቻችን የሰላምን ጥሪ እንዲቀበሉ ለማድረግ በጋራ መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል።
ሰላምን ማረጋገጥ ከቻልን የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ጊዜ አይፈጅም ያሉት ዶክተር ዘሪሁን የሚታየው የጎንደር ከተማ የልማት ሥራ ገና ጅምር በመኾኑ ወደፊት ሰላሙ ከሰፈነ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማከናወን ገልጸዋል።
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል የሰላሙን ሁኔታ ለማሻሻል የሕግ ማስከበር ሥራ ብቻ በቂ አለመኾኑን ጠቅሰው በማኅበራዊ ሚዲያ የሚንሸራሸሩ ሀሳቦችን መፈተሽ እና መገምገም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም ሁሌም በሩ ክፍት ነው ያሉት ሚኒስትሯ በየትኛውም ቦታ ያሉ አካላት የሰላም አማራጭን በመጠቀም እየተቃጣ ያለውን የውጭ የግጭት አዙሪት መሰበር እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያ የማደግ አቅሟ በዓመት 2 ነጥብ 6 መድረሱንም ገልጸዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ በ68 ከተሞች የኮሪደር ልማት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ነው ያስረዱት።
የሥራ ዕድልን ለማሳደግ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገር ትስስር እየተፈጠረ መኾኑን ገልጸው በሀገር ውስጥ እየተሰጠ ያለው የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና የበርካታ ሥራ አጥ ወጣቶችን ችግር የሚቀርፍ መኾኑንም አንስተዋል።
የጎንደርን የልማት ሥራ ከፍ ለማድረግ የሕዝብ ተሳትፎ እና እገዛ በእጅጉ እንደሚያስፈልግ በውይይት መድረኩ ተመላክቷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የጎንደር ከተማን ልማት ለማረጋገጥ መንግሥት የጀመረውን የኮሪደር ልማት አጠናክሮ መቀጥል እንደሚገባው ተናግረዋል።
የከተማዋን ነዋሪዎች ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የፋብሪካ እና ሌሎች ከፍተኛ ፕሮጀክቶች እንዲስፋፉ እና የኑሮ ውድነትን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።
ሰላምን ለማረጋገጥም ኾነ፣ ልማትን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት ሁሉ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አሳውቀዋል።
ዘጋቢ:- ተስፋየ ጋሹ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
