“አሁን ላይ ሰላማችሁን በራሳችሁ እንደምታረጋግጡ እናምናለን” ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

5

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኀላፊዎች ከፍኖተ ሰላም፣ ከጅጋ ከተማ እና ከጃቢ ጠህናን ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በፍኖተ ሰላም ከተማ ተወያይተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ከተፈለገ ሕዝብ የሰላም ችግር መነሻ ምክንያትን በሐቅ መናገር እና መፍትሔ ማመላከት ይጠበቅበታል ብለዋል።

እናንተ ሐቅን ተናግራችኋል፤ ግፍን አውግዛችኋል የሚጠበቀው ይህ ነው ብለዋል። በምዕራብ ጎጃም ዞን ግፍ መፈጸሙን አንስተዋል። የተፈጠረው ግፍ ከሕዝብ ባሕል እና እሴት ያፈነገጠ መኾኑን ተናግረዋል።

ሥርዓተ መንግሥት አንዲጠናከር መሥራታችሁ፤ ያለ መንግሥት ሀገር እንደማይጸና ግልጽ አቋም መያዛችሁ ሰላምን ለማረጋገጥ መሠረት ነው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት የነበሩ የአስተውሎት እና የስክነት ችግሮች እየተቀረፉ መኾናቸውን ገልጸዋል። በሕዝብ ላይ ችግር እንዲፈጠር ያደረገው የአስተውሎት እና የስክነት ችግር ነው ብለዋል። ችግሩ ገብቷችኋልና አሁን ላይ ሰላማችሁን በራሳችሁ እንደምታረጋግጡ እናምናለን ብለዋል። ሕዝብን በሚያማርሩ መሪዎች እና ባለሙያዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ተናግረዋል።

የአካባቢው ባለሃብቶች አካበቢያችሁን ማልማት አለባችሁ፤ በደጉ ጊዜ ሃብት ያፈራችሁበትን አካባቢ በችግሩ ጊዜ ጥላችሁ መሄድ ሕዝብን እንደመካሄድ ይቆጠራል ነው ያሉት። ወደ ጀመሩት ሥራ መመለስ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ታጣቂዎችን በሃብት የሚደግፉ ባለሃብቶች ደግሞ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። በዚህ ድርጊት ውስጥ በተጨባጭ በሚገኙ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም አስገንዝበዋል።

ሰላምን ለማረጋገጥ እየሠሩ ያሉ የሃይማኖት አባቶች መልካም ተግባራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የጠየቁት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ከሃይማኖት አስተምህሮ ውጭ ግጭትን የሚያባብሱ እና ጽንፈኝነትን የሚደግፉት ግን መታረም አለባቸው ነው ያሉት።

ጫካ የገቡ አካላት ከጠላት ጋር የተሰለፉ የአማራን ሕዝብ የሚያሳንሱ ናቸው ብለዋል። ይህን ሀገርን የሚያሳንስ ቡድን ማውገዝ እና መታገል ይገባል ነው ያሉት። መሪዎች ሕዝብን በማደራጀት ለሰላም እና ለልማት እንዲሠሩም አሳስበዋል።

ውስጣቸውን እንዲያጠሩ እና በወጥ አቋም እንዲሠሩም አሳስበዋል። የጸጥታ ኃይሉን ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በልማት እና በትርፍ አምራችነቱ የሚታወቀውን የቀደመውን ጎጃም መመለስ እንደሚገባም ተናግረዋል።

መንግሥት ለሰላም አማራጭ ቅደሚያ በመስጠት እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ለሰላም በተሰጠው አማራጭም ለውጥ መገኘቱን አስታውቀዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጽንፈኞች በደረሰባቸው ምት በዋሉበት ማደር ወደማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል” ሌትናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ
Next articleተባባሪ የኾነው የጎንደር ሕዝብ በልማት ሥራዎች ላይ የበኩሉን እየተወጣ ነው።