
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌትናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ከፍኖተ ሰላም፣ ከጅጋ ከተማ እና ከጃቢ ጠህናን ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በፍኖተ ሰላም ከተማ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ላይ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ዕድሜዓለም አንተነህ፣ የኮር አዛዥ የኾኑት ብርጋዴር ጄኔራል መላኩ ገላነህ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት ሌትናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ሠራዊታችን ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር በመኾን ጽንፈኛውን በጸረ ሽምቅ አሳዶ በመምታት በአሁኑ ሰዓት አንጻራዊ ሰላም አምጥቷል ብለዋል። ይህንን የዜጎች መሠረታዊ ሃብት ዘላቂ ለማድረግ ሕዝቡ የሰላሙ ባለቤት ኾኖ ቀን ከሌት መሥራት አለበት ነው ያሉት።
ሌትናል ጄኔራል መሐመድ እንዳሉት በአባቶቻችን እና በአሁኑ ትውልድ የተሸነፉት የኢትዮጵያ ጠላቶች የውክልና ጥቃት የሚከፍቱ ባንዳዎችን በመመልመል፣ በማሠልጠን፣ በማስታጠቅ እና ሎጀስቲክ በማሟላት ሀገራችን እንድትተራመስ የሚያደርጉት ጥረት መክሸፉን ተናግረዋል።
የጎጃም ሕዝብ ይህ የተልዕኮ ውጊያ መኾኑን በመረዳት ያገኘውን ሰላም የተሟላ ለማድረግ ከምንም ነገር በፊት መሰለፍ ይኖርበታል ብለዋል።
ጽንፈኞቹ ከግብጽ፣ ከኤርትራ እና ከሕውሀት ጋር የጋራ ሰነድ አዘጋጅተው ኢትዮጵያን ለመውጋት ቢሰማሩም በአሁኑ ሰዓት “በደረሰባቸው ምት በዋሉበት ማደር ወደማይችሉበት ደረጃ ተመናምነዋል” ነው ያሉት።
እነዚህ ብረት ነካሾች የሀገርን ሉዓላዊነት ለባዕዳን አሳልፈው የሚሰጡ፣ ፀረ ኢትዮጵያ እና ፀረ አማራ የኾኑ፣ ይህ ነው የሚባል የአማራን ሕዝብ ጥያቄ የሚመልስ ፕሮግራም እና ስትራቴጂ የሌላቸው፤ የራሳቸውን ሕዝብ የሚበሉ ናቸው ብለዋል።
የአሁኖቹ ባንዳዎች በውጊያ ተቀጥቅጠው ሲሽመደመዱ በመንደር አስተሳሰብ፣ በጥቅም፣ በዘረኝነት እና በሙሰኛ መሪዎች በመደገፍ የጋላቢዎቻቸውን ፍላጎት ለማሳካት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ሕዝቡ በንቃት ተከታትሎ እንዲታገላቸው ማሳሰባቸውን ከምስራቅ ዕዝ ሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
