ማኅበረሰቡ እና መሪዎች ተቀናጅተው በመሥራታቸው ጥላቻን ነቅሎ ሰላም እና ፍቅርን መትከል ተችሏል።

2

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከሸዋሮቢት፣ ከኤፍራታ ግድም፣ ከጅሌ ጥሙጋ፣ ከሰንበቴ እና አካባቢው የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በጀውኃ ከተማ በሰላም እና ልማት ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።

የሸኔ ኃይሎች እና ጽንፈኞች በሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አጎራባች ወረዳዎች በፈጠሩት ጥላቻ ከሁለት ዓመት በፊት በአካበቢው ላይ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት መድረሱን በውይይቱ ተገልጿል።

መንግሥት እና ማኅበረሰቡ ባደረጉት የተጠናከረ የሰላም ማጽናት ተግባር የሁለቱ አካባቢ ሕዝቦች የነበረው ማኅበራዊ መስተጋብር እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር መመለሱን አንስተዋል።

ነዋሪዎቹ የመብራት፣ መንገድ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እንዲፈቱላቸውም ጠይቀዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ ሰውነትን በማስቀደም እና አብሮነት ላይ በመሠራቱ ከሰላም ማጣት በመውጣት ወደ መልማት ጥያቄ መሸጋገር ተችሏል ብለዋል። በቀጣይም አስተማማኝ ሰላም በመዘርጋት የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እንሠራለን ነው ያሉት።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ “ማኅበረሰቡ እና መሪዎች ተቀናጅተው በመሥራታቸው ጥላቻን ነቅሎ ሰላም እና ፍቅርን መትከል ተችሏል” ብለዋል። ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል በወንድማማችነት እና አህትማማችነት መንፈስ እየሠሩ መኾናቸውንም አስረድተዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ተደናቅፎ የቆየውን የመልማት ጸጋ ወደ ልማት ለማስገባት እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው ብለዋል።

በአካባቢው አልፎ አልፎ የሚታየውን የሰላም እጦት ወደ አስተማማኝ ሰላም ለማስገባት ማኅበረሰቡ በተለይ ወጣቶች በጠራ አመለካከት ለአንድነት እና አብሮነት መሥራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleደብረ ብርሃን ከተማ የኢንቨስትመንት ፍሰትን በአግባቡ በመጠቀም ለውጥን መሬት ላይ በማሳየት ተምሳሌት ናት።
Next article“ጽንፈኞች በደረሰባቸው ምት በዋሉበት ማደር ወደማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል” ሌትናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ