ደብረ ብርሃን ከተማ የኢንቨስትመንት ፍሰትን በአግባቡ በመጠቀም ለውጥን መሬት ላይ በማሳየት ተምሳሌት ናት።

0

ደብረ ብርሃን: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደብረ ብርሃን ከተማ ተገኝተው የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጽያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኀላፊ ማስረሻ በላቸው፣ በኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ከንቲባ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሥራ አሥፈጻሚ አባል ተሾመ አዱኛ (ዶ.ር)፣ የሰሜን ሸዋ ዞን እና የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በጉብኝታቸው የዴዴ ጠርሙስ ፋብሪካን፣ ብራውን ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካን እና በጣይቱ ክፍለ ከተማ ልቼ ቀበሌ በሕዝብ ተሳትፎ የተገነቡ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።

ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማስረሻ በላቸው ደብረ ብርሃን ላይ ያየነው ልማት ሀገራችን የምታካሂደው የለውጥ መንገድ ማሳያዎች ነው ብለዋል።

ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንደስትሪያላይዜሽን ለሚደረገው ሽግግር አሁን ከተማዋ እያለፈችበት ያለው እድገት ብርቱ አቅም የሚፈጥር መኾኑን ተመልክቻለሁ ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳደሩ፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚለማው ሰብል 65 በመቶ የሚኾነው የበቆሎ ምርት ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳደሩ ያም ኾኖ ያን ያህል ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

አሁን ላይ ደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኘውን የብራውን ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካን መመልከታቸው በቀጥታ ለምርቱ ትስስር በመፍጠር አምራቾቹን እና ፋብሪካውን ማገናኘት የሚቻልበት ዕድል መኖሩን ተናግረዋል።
በቆሎን አርሶ አደሮቻችን በስፋት እንዲያመርቱ የሚያስችል ፋብሪካ አይተናል ነው ያሉት።

ታሪካዊቷ ደብረ ብርሃን ከተማ ምን ያህል የኢንዱስትሪ ከተማ እየኾነች እንደመጣች ተገብዝበናል ያሉት ሌላኛው የጉብኝቱ ተሳታፊ በኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ከንቲባ እና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሥራ አሥፈጻሚ አባል ተሾመ አዱኛ (ዶ.ር) ናቸው።

የበቆሎን ምርት በግብዓትነት ተጠቅሞ ወደ ተለያዩ የምግብ ምርቶች የሚቀይረውን ፋብሪካ ማየታቸው ትልቅ ተሞክሮ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

የከተሞች መሪዎች ልምድ ልውውጥ ማድረግ ካለባቸው ደብረ ብርሃን ከተማን ቀዳሚ ምርጫቸው ቢያደርጉ የተሻለ ተሞክሮ መውሰድ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

ከአካባቢያችን ወጣ ብለን የሌሎች ከተሞችን እድገት በተሞክሮነት መቀመር አለብን ያሉት ከንቲባው የኢንቨስትመንት ፍሰትን በዘላቂነት ማስጠበቅ ከቻለችው ደብረ ብርሃን ብዙ ልምዶችን ወስደናል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ:- ወንዲፍራ ዘውዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleገዳ ባንክ በበጀት ዓመቱ 342 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አገኘ።
Next articleማኅበረሰቡ እና መሪዎች ተቀናጅተው በመሥራታቸው ጥላቻን ነቅሎ ሰላም እና ፍቅርን መትከል ተችሏል።