
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም የክልል እና የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ መሪዎች “የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች ” በሚል መሪ መልዕክት በወቅታዊ ክልላዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ በደሴ ከተማ ከልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እያደረጉ ነው።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አወሉ አብዲ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሀ ደሳለኝ፣ የከተማ አሥተዳደሩ እና የዞኑ መሪዎች በመድረኩ ተገኝተዋል።
የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ተወካዮች በውይይቱ እየተሳተፉ ነው።
የውይይቱ ተሳታፊ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ከተማችን ደሴ ሰላማዊ ነች፤ መሪዎቿ እና ነዋሪዎቿ አንድ ኾነው እያለሟት ያለች ከተማም ናት ብለዋል። በሰላማዊ ከተማ ውስጥ ውዥንብር የሚነዙ አፍራሾች መኖራቸው የማይካድ ቢኾንም የደሴን ሕዝብ አንድነት እና ፍቅር መናድ ግን አይቻላቸውም ነው ያሉት።
ወሎ አንዱ ላንዱ የቆመ፣ እስላም ክርስቲያኑ በጋራ ያለልዩነት የሚወዳቸው መሪዎች እና የሃይማኖት አባቶች ያሉት ሕዝብ መኖሪያ ነውም ብለዋል።
የወሎ ሕዝብ ፍቅር፣ አንድነት እና ሰላም ወዳድነት ጥልቅ ነው፤ ሁሉን ወዳዱ አባ መፍቅሬ ሰብ እና የሁሉም አባት የነበሩት ሼሕ መሐመድ ገታ ልዩ የጋራ ምልክቶቻችን ናቸው ብለዋል።
አብሮነት ጌጣችን ነው፤ እጅ ለእጅ ተያይዞ በደሴ አደባባይ ላይ የቆመ የአባ መፍቀሬ ሰብ እና የሼሕ መሐመድ ገታን ሐውልት ማየት እና አንድነታችንን ለዓለም ማሳየት ነው የምንሻው ብለዋል ነዋሪዎች።
በማኅበራዊ ሚዲያ በሬ ወለደ ወሬ የከተማዋን መሪዎች በማብጠልጠል ሰላማችንን ለማናጋት እና በመንግሥት የተጀመሩ ልማቶችን ለማጓተት የሚጥሩ አጥፊዎችን አንቀበልም ሲሉም ተናግረዋል።
ከተማ ውስጥ ተቀምጠው ወሬ የሚያናፍሱትም ኾነ ታጥቀው ጫካ ውስጥ የገቡት የሕዝብን ጥያቄ ማስመለስ አይችሉምና መስከን አለባቸው ብለዋል።
መሪዎችን፣ ለሕዝ የሚሠሩ የተለያዩ ግለሰቦችን እና የሃይማኖት አባቶችንም ጭምር በማብጠልጠል የተጠመዱ አካላት አሉ፤ ከሕዝብ ዕይታ ስለማያመልጡ ፈጥነው ከድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው ነው ያሉት ነዋሪዎች።
ደሴ በርካታ የልማት ትሩፋቶች አሉ፣ ታይቶ የማይታወቅ የኮሪደር ልማትም እየተከናወነ ይገኛል፤ እነዚህን ልማቶች እየደገፍን ቀሪ ልማቶችንም በስክነት ከመሪዎቻችን እንጠይቃለን ነው ያሉት።
የመንግሥት የበዛ ሆደ ሰፊነት በመጠቀም የሚንቀሳቀሱ አካላት ሕገወጥነትን እያስፋፉ መኾኑን በውል መረዳት እና ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ መከናወን እንዳለበትም ተሳታፊዎች አንስተዋል።
የደሴ ከተማን ታሪክ የሚመጥን እና ተከታታይነት ያለው የመሰረተ ልማት ግንባታ እንዲከናወንም የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል። የኮምቦልቻ – ደሴ የመንገድ ግንባታ እንዲጀመርም ተጠይቋል። ከአዋሽ – ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ ተጀምሮ ያልተጠናቀቀው የባቡር መንገድ ቀሪ ሥራዎች ተጠናቅቀው ለፍጻሜ ይብቃልን ሲሉም ጠይቀዋል ነዋሪዎች።
የኑሮ ውድነት በተለይም አቅም የሌላቸውን ዜጎች መፈተኑም በተሳታፊዎች ተነስቷል። መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ዜጎችን በትክክል ተደራሽ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ነድፎ መሥራት እንዳለበትም ተነስቷል።
ሕዝብን ከሕዝብ ከማቀራረብ ይልቅ የሚለያዩ፣ ለኢትዮጵያውያን ወንድማማችነት መጽናትም እንቅፋት የሚኾኑ አሉታዊ ትርክቶችን ፈጥኖ መለየት እና ማስተካከል እንደሚገባም የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል።
አንድነትን የሚሸረሽሩ እና የጥላቻ ትርክትን የያዙ ሐውልቶችን መንቀል እና በአንድነት እና ፍቅር ሐውልቶች መተካት ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
