
ደብረ ማርቆስ: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሲሰጥ የቆየው የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጎጃም ቀጣና ፖሊስ መሪዎች እና አባላት የጂኦ ስትራቴጂክ እና የአመራር አቅም ግንባታ ሥልጠና ተጠናቅቋል፡፡
በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ ሥልጠናው የነበሩ ችግሮች በአግባቡ የተለዩበት ነው ብለዋል።
የፖሊስ መሪዎች እና አባላት እንደ ክልል እና እንደ ሀገር ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁ ለመኾን የሚያስችል ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡
“ማኅበረሰቡን ያላቀፈ የወንጀል መከላከል ሥራ ውጤታማ ሊኾን አይችልም” ያሉት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እና በመረጃ የተደገፈ የመሪ ተግባር መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ግዛቸው ከበደ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እያከናወናቸው የሚገኙ የለውጥ ተግባራትን አድንቀዋል። ለፖሊስ መሪዎች እና አባላት ከማስገንዘብ ባለፈ የጸጥታ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ታልሞ ሥልጠናው መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
ብቃት ያለው ሙያዊ ሥነ ምግባርን አክብሮ የሚሠራ እና ክልሉ ካጋጠመው የሰላም እጦት እንዲወጣ የሚያስችል ቁመና ላይ መገኘት ከፖሊስ መሪዎች እና አባላት የሚጠበቅ ተግባር መኾኑንም አብራርተዋል፡፡
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ግርማ ጫኔ በተቋማዊ የለውጥ ሥራዎች የተገኙ ውጤቶች እና በቀጣይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈተናዎች ለመለየት አቅም የፈጠረ ሥልጠና ስለመኾኑ አመላክተዋል፡፡
ኅብረተሰቡ ካጋጠመው ግጭት ተላቆ ሰላማዊ ኑሮውን እንዲቀጥል ለማስቻል በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ እና የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰበት ሥልጠና ነበር ብለዋል፡፡
የሥልጠናው ተሳታፊዎች ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ ምግባር በመላበስ ኅብረተሰቡን አቅፎ መሥራት ከተቻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያሳየ እና ቁጭት የፈጠረ ሥልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡
አሁን እየታየ ያለውን አንጻራዊ ሰላም የተሟላ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ዝግጁ መኾናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
