
ፍኖተ ሰላም: ታኅሣሥ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተቀናጀ የፖሊዮ መከላከያ ክትባት በምዕራብ ጎጃም ዞን እየተሰጠ ይገኛል። ክትባቱ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለኾኑ ሕጻናት ነው የሚሰጠው።
የፖሊዮ በሽታ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ቀድመው በመረዳት ልጆቻቸውን እያስከተቡ መኾናቸውን በፍኖተ ሰላም ከተማ የሚገኙ እናቶች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የበሽታውን አስከፊነት በመረዳት ሁሉም እናቶች ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡም መክረዋል።
በፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ለተከታታይ ቀናት ከ9 ሺህ 200 በላይ ለሚኾኑ ሕጻናት ክትባት እንደሚሰጥ የተናገሩት በከተማ አሥተዳደሩ ጤና ጽሕፈት ቤት የኅብረተሰብ አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ባለሙያ አዝመራው አዳሙ ናቸው።
ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን በማከናወን ክትባቱ በዘመቻ እየተሰጠ መኾኑን አስረድተዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለኾኑ ከ242 ሺህ በላይ ሕጻናት ክትባት ለመስጠት ታቅዶ እየተከናወነ መኾኑን የዞኑ ጤና መምሪያ ኀላፊ ኤፍሬም ክፍሌ ተናግረዋል።
አስፈላገው ግብዓት ለወረዳዎች ተደራሽ ተደርጎ ክትባቱ እየተሰጠ መኾኑን ነው የገለጹት።
ኅብረተሰቡ ሕጻናትን በማስከተብ እና “የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል እየተሠራ ባለው ተግባር እገዛ እንዲያደርግም” ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
