
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 03/2018ዓ.ም (አሚኮ) ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ማንኛውም ነዋሪ ራሱን የሚገልጽበት እና መብቱን የሚያረጋግጥበት መለያ ነው።
የዐይን፣ የፊት እና የጣት አሻራን ከግል መረጃ ጋር በማቀናጀት ኢትዮጵያ ላይ የሚኖር ከአምስት ዓመት ጀምሮ ያለ ማንኛውም ዜጋ ያለመከልከል የሚያገኘው መለያ ነው።
በብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ውስጥ የሥልጠና ክፍል ኀላፊ ናኦል ከበደ በኢትዮጽያ የሚገኙ ሁሉም ነዋሪዎች ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያን እንዲጠቀሙ የተፈለገበት ምክንያት እንደ ሀገርም ኾነ እንደ ግለሰብ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ስለኾነ ነው ብለዋል።
ከብሔራዊ መታወቂያ ውጭ ያሉት ሌሎች መታወቂያዎች ሰዎችን የሚያጉላሉ እና በየተቋማቱ ለአንድ አገልግሎት በርካታ ሰነዶች የሚጠየቁበት ሁኔታ እንዳለው ጠቅሰዋል። ብሔራዊ መታወቂያ ግን 12 አሀዝ ቁጥሩን በመንገር ብቻ በማንኛውም ቦታ የተለያየ አገልግሎት በቀላሉ በአንድ ጊዜ ለማግኘት እንደሚያስችል ነው የገለጹት ።
ሀገርስ ምን ትጠቀማለች? በሚል አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ላነሳንላቸው ጥያቄ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ እንደ ሀገርም ኾነ እንደ ግለሰብ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
ከጠቀሜታዎቹ ውስጥ:-
ዜጎች ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያን በአስገዳጅ ሁኔታ እንዲያወጡ ይገደዳሉ?
ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ዜጋ እንዲጠቀም አስገዳጅ ሕግ የለም ያሉት ናኦል ከበደ ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ጋር ስለሚያያይዟቸው ማኅበረሰቡ እንዳይጉላላ እና ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኝ ብሔራዊ መታወቂያ እንዲመዘገቡ መክረዋል።
ተቋማት አገልግሎት ፈልገው ወደ እነሱ የሚሄዱ ተገልጋዮች ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያን የመጠየቅ ሥልጣን እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል። አሁን ላይም በርካታ ተቋማት ወደዚህ አሠራር እየገቡ ነው፤ ቀጣይ ሁሉም ተቋማት ወደ አሠራሩ ይገባሉ ብለዋል።
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያን ተግባራዊ ያላደረጉ ሀገራት የሚያጡት ነገር ጋር በተያያዘም በሀገር ላይ የማንነት መጭበርበር ገዝፎ ይታይባቸዋል ነው ያሉት።
ሀገርን በተለያዩ ዘርፎች ወደ ኋላ ያስቀራል፤ ከሌሎች ሀገሮች ጋር መወዳደር አያስችልም ብለዋል።
ዲጂታል መታወቂያን ተግባራዊ አለማድረግ የነዋሪዎችን የአገልግሎት ተጠቃሚነት ያዛባል፤ አገልግሎት ፈላጊ ነዋሪዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዳያገኙ ያንገላታልም ነው ያሉት።
በቅርብ ጊዜ የተደረገን ጥናት ጠቅሰውም ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያን በመጠቀም ተግባራዊ ያደረጉ ሀገራት በአምስት እጥፍ የጂዲፒ እድገት እስከማሳደግ የደረሱ እንዳሉም ጠቁመዋል።
በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ምዝገባውን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ነው የነገሩን።
አሁን ላይ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ መመዝገቢያ ማሽን እና የምዝገባ ባለሙያዎችን በየቦታው በማኅበረሰቡ አቅራቢያ ለማዳረስ ጥረት ስለተደረገ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ለማግኘት መመዝገብ ለሚፈልግ ሰው የት ሂጀ ልመዝገብ የሚለው ጉዳይ ጥያቄ እንደማይኾንም ነው ያነሱት።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
