
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እንስሣት እና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ በክልሉ እያከናወናቸው ካሉት ተግባራት መካከል የሌማት ትሩፋት አንዱ ነው።
ቢሮው በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ለብዙኀን መገናኛ ተቋማት እያስጎበኘ ነው።
የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ መክያ ሁሴን ለ10 ዓመታት ያክል በስደት በአረብ ሀገር እንደኖሩ ነግረውናል። በአሁኑ ሰዓት መንግሥት በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ያመቻቸላቸውን እድል ተጠቅመው በዶሮ ርባታ ተሠማርተው ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ወይዘሮ መክያ እንደሚሉት በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር አማካኝነት በዶሮ ርባታ ዘርፍ ከተሰማሩ ከሁለት ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል። በ500 የዶሮ ጫጩት ተነስተው በአሁኑ ሰዓት 1 ሺህ 500 ያህል ዶሮዎችን የማርባት አቅም ላይ መድረሳቸውን ነው የገለጹት።
የከተማ አሥተዳደሩ ባመቻቸላቸው የመሥሪያ ቦታ እየሠሩ ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን እያሥተዳደሩ እንደሚገኙም ነው የገለጹት። ነጻነነትን አጥቶ በባዕድ ሀገር በስደት ከመኖር ይልቅ በነጻነት በሀገር ሠርቶ መለወጥ እንደሚቻልም ገልጸዋል።
በዶሮ ርባታ ዘርፍ የተሠማራው ሌላኛው ወጣት ዮናታን ብርሃኑ ደግሞ በእንስሳት ሕክምና የመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል።
በወጣቶች የተዘዋዋሪ ፈንድ ተጠቃሚ በመኾን በ150 ሺህ ብር ከጓደኞቹ ጋር ወደ ሥራ ገብተዋል። በ1 ሺህ 500 ጫጩት ጀምረው በአሁኑ ሰዓት 5 ሺህ የእንቁላል ጣይ ዶሮ እንዳሏቸው እና ከ16 ሺህ በላይ ጫጩቶች እንዳሏቸው ገልጸዋል። ከራሳቸው አልፈውም ለ15 ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር እንደቻሉ ያስረዳሉ።
በትንሽ ቦታ ብዙ ዶሮ ማርባት በሚያስችል ቴክኖሎጅ እየተጠቀሙ መኾኑን አብራርተዋል። የእንስሣት ሃብት ጽሕፈት ቤት አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው አንስተዋል። ተጨማሪ የማስፋፊያ ቦታ ከተማ አሥተዳደሩ እንዲያመቻችላቸውም ጠይቀዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር እንስሣትና ዓሣ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መሐመድ አሊ በከተማዋ ሰፊ የሌማት ትሩፋት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ውጤት እያመጡ መኾኑንም ጠቁመዋል።
በእንቁላል ዶሮ 23 ኢንተርፕራይዞች፣ በአንድ ቀን ጫጬት ማሳደግ 44 ኢንተርፕራይዞች፣ በኢንቨስትመንት ደረጃ ደግሞ ሁለት ባለሃብቶች በዘርፉ ተሠማርተው በስፋት እየሠሩ ነው ብለዋል።
በዘርፉ ለተሰማሩ አርቢዎች ከአመራሩ ጋር በመነጋገር የመሥሪያ ቦታ እንዲመቻችላቸው በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በከተማዋ በዘመናዊ መንገድ በክላስተር እንዲተገበር በእቅድ ተይዞ እየተሠራ ስለመኾኑም ጠቁመዋል። ከዶሮ እንቁላል ባለፈ የዶሮ ስጋን በማቀነባበር ለማቅረብ በእቅድ መያዙን አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
