
ገንዳ ውኃ: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን የሥራ አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት የንቅናቄ መድረክን በገንዳ ውኃ ከተማ አካሂዷል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ ጤናማ እና አምራች ኃይል ለማፍራት ማኅበረሰቡን የጤና መድኅን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻልም እንደ ዞን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል። ማኅበረሰቡን የጤና መድኅን አባል በማድረግ መሪዎች ኀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ጅብሪል መርሻ በዞኑ ባለፈው ዓመት ከ51 ሺህ በላይ የሚኾኑ አባወራዎችን የማኅበረሰብ ጤና መድኅን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በዚህ ዓመትም ከ89 ሺህ በላይ አባወራዎችን የጤና መድኅን ተጠቀሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
በዓመቱም በጤና መድኅን ከ250 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች መታከማቸውን ገልጸዋል። የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት እና አሠራርን ለማሻሻል ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታትም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑንም አስረድተዋል።
ሁሉም የጤና መድኅን አባላት ክፍያውን በወቅቱ በመክፈል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መኾን እንዳለበት ኀላፊው መልዕክት አስተላልፈዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ ስጦታው አዱኛ የዘንድሮው የጤና መድኅን አገልግሎት ለማስጀመር በርካታ ተግባራት ሢሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል። ፍትሐዊ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
አገልግሎቱን ለማሻሻል በየጊዜው በመገምገም ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል።
ሌላኛው ተሳታፊ አቶ አብነት ደሴ በወረዳው የመድሃኒት አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የማኅበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ ለመገንባታ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡን መሉ በሙሉ የጤና መድኅን ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ የሕዝብ ለሕዝብ ውይይቶች መደረጋቸውንም ገልጸዋል።
ከማኅበረሰቡ ተጠቃሚነት ባለፈ በቀጣይ የመንግሥት ሠራተኛውን የጤና መድኅን ተጠቃሚ ለማደረግ ይሠራል ያሉት ደግሞ አቶ ፋሲል አድማሱ ናቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
